የኢቢቪ ዘጋቢ፣ ዋሽንግተን ዲሲ
መንግስት በኢራን እና አሜሪካ ወ እስራኤል መካከል ባለው የግጭት ሁኔታ በባህረ ሰላጤው የተፈጠረው ችግር በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ላይ ጫና እንዳያሳርፍ መስጋቱን መንግስት አስታወቀ፡፡
በአለም ባንክ እና አለምአቀፍ የገንዘብ ድርጅት የመፀው ወቅት ስብሰባ የታደሙት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዥ ዶር እዮብ ተካልኝ እንደገለጹት የባህረ ሰላጤው ግጭት እና የሆርሙዝ ሰርጥ መዘጋት በኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳው ላይ ጥላ አጥልቷል ሲሉ ገልጸዋል
ቀደም ሲል የኢኮኖሚ ባለሞያዎች ነዳጅ እና ማዳበሪያ አቅርቦት በሆርሙዝ ሰርጥ መዘጋት ሳቢያ መስተጓጎሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያው ላይ ጫና እንደሚኖረው መግለጻቸውን ቅዳሜ ገበያ በሬድዮ ስርጭት ወቅት ማቅረቧ ይታወሳል፡፡
ዶር እዮብ የወቅቱን ሁኔታ ከባድ ጊዜ ሲሉ ነው የገለፁት፡፡ እንዲያም ሆኖ ማሻሻያውን ከሚደግፉት ከአጋሮች ጋር በመተባበር እና በመግባባት ሁኔታው የሚፈጥረውን ጫና ለማጣጣም እና ማሻሻያው ግቡን እንዲመታ ለማስቻል ንግግር መጀመሩን ገልፀዋል፡፡
ይሄን ችግር እንዴት አልፈን የረጅም ጊዜ ግባችንን እናሳካ የሚለው ላይ ነው ትኩረቱ ያሉት ገዥው፡፡ ብልጠት የታከለበት የችግር መውጫ መፍጠር እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት፡፡
ኢትዮጵያ በ2017 ዓም የጀመረችው የአራት አመት የኢኮኖሚ ማሻሻያ በአለም ባንክ እና የገንዘብ ተቋሙ በገንዘብ ጭምር የሚደገፍ መሆኑ ይታወሳል፡፡
በማሻሻያው አጋሮች ድጋፍ ለማድረግ ከኢትዮጵያ መንግስት የሚጠብቁት አንዳንድ ለውጦች መሆኖሩ ይታወሳል፡፡ ከነዚህ መካከል የነዳጅ ድጎማ ማላላት፣ የመንግስት ገቢ ማሳደግ እና ኢኮኖሚውን ለውጭ ተዋንያን መክፈትን ጨምሮ የውጭ ምንዛሬ አስተዳደሩን በመሰረታዊነት መቀየር የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ሆኖም የወቅቱ ሁኔታ መንግስት በተለይ ከውጭ ምንዛሬ ፍላጎት፣ ከዋጋ ግሽበት እና መሰል ሁኔታዎች አንፃር ጫና እንዳይፈጠር አንዳንድ ማሻሻያዎችን ሊያዘገይ እንደሚችል በባለሞያዎች ይገመታል፡፡
ለምሳሌ በበጀት አመቱ ለነዳጅ የሚደረገው ድጎማ ከ100 ቢሊየን ብር እንደማይበልጥ ለአጋሮች የተገለፀ ቢሆንም ከወዲሁ 270 ቢሊየን ብር ለነዳጅ መደጎሙን መንግስት አስታውቋል፡፡
በተመሳሳይ እየወረደ የሚገኘው የዋጋ ግሽበት ተመልሶ እንዳያድግ ለመቆጣጠር አንዳንድ እርምጃዎች ሊወሰዱ እንደሚችሉ ነው የሚገመተው፡፡©SECO

