ኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት የደረጃ 3 (ML3) ያገኘች 9ኛዋ የአፍሪካ ሀገር ከሆነች በኋላ፣ በሀገር ውስጥ ምርት አሁን ላይ ከ40 በመቶ በላይ የሕክምና አቅርቦትን እየሸፈነች ነው።
የዓለም ባንክ ቡድን (WBG) ኢትዮጵያን በማስመልከት ያወጣው ልዩ ዘገባ እንደሚያሳየው በቂሊንጦ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን፣ እንዲሁም በAHRI እና CDT-Africa የሚደረጉ ምርምሮች ውጤት እያስገኙ ነው።
ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት ባለሥልጣን (IGAD) ቀጠና የመጀመሪያዋ፣ እንዲሁም በአፍሪካ ዘጠነኛዋ ሀገር በመሆን ለመድኃኒት ቁጥጥር የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) Maturity Level 3 (ML3) ደረጃን ስታገኝ የተደረገው ምርምርና የተገኘው ውጤት ጉልህ ሚና እንደነበረው ተጠቁሟል፡፡
የተገኘው ስኬትም የኢትዮጵያ የቁጥጥር ሥርዓት ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን እንደሚያሟላ እንደሚያረጋግጥ ቡድኑ አስታውቋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ሀገራት መድኃኒቶችን፣ ክትባቶችን እና ሌሎች የሕክምና ምርቶችን እንዴት እንደሚቆጣጠሩ ለመገምገም ከ250 በላይ አመልካቾችን የያዘ ዓለም አቀፍ የመለኪያ መሣሪያን የሚጠቀም ሲሆን እነዚህ አመልካቾች ሙሉውን የቁጥጥር ሂደት ያጠቃልላሉ – ከማጽደቅ እና ከቁጥጥር እስከ ጥራት ምርመራ፣ ከገበያ በኋላ ክትትል እና የአስተዳደር ሥርዓቶች። በኢትዮጵያ ውስጥ እነዚህ ሥርዓቶች አሁን ከዓለም አቀፍ ደረጃዎች ጋር የተጣጣሙ እና በተቀናጀ መንገድ እየሰሩ እንደሚገኙ ታውቋል።
ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ከውጭ በሚገቡ መድኃኒቶች ላይ ተመርኩዛ ቆይታለች። ያ አካሄድ አሁን መለወጥ ጀምሯል ሲል ቡድኑ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ የፋርማሲዩቲካል ዘርፍ በአብዛኛው ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ጥገኛ ከነበረ ኢንዱስትሪ ወደ ተለያዩ የጤና እንክብካቤ ማምረቻ መሠረቶች እየተሸጋገረ እንደሆነ ተጠቁሟል።@seco


