በአለምሰገድ እስጢፋኖስ
በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ማሻሻያዎች፣ ካፒታላይዜሽን፣ ውህደትና የተቋማት ግዚዎች፣የባለአክሲዮኖች ሚና በሚል ዘመን ባንክ ያዘጋጀው የፓናል ውይይት ተካሄደ
የፓናል ውይይቱ በባንኮች፣ በተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤቶች፣ በባለድርሻ አካላት እና በባለአክሲዮኖች መካከል የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር፣ ልምድ ለመለዋወጥና ወደፊት የሚወሰዱ ስትራቴጂያዊ አቅጣጫዎችን ግብዓት ለመስጠት ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡
በፓናል ውይይቱ ላይ የዘመን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደረጀ ዘበነ
እንዳስታወቁት ተለዋዋጭ የሆነው የዓለም አቀፍና የሀገራችን ኢኮኖሚ እድገት፣ የገበያ መስፋፋት፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችና የፖሊሲ ማሻሻያዎች ባንኮችን የበለጠ ጠንካራ፣ ተወዳዳሪና ብቁ ሆነው እንዲገኙ ያስገድዳል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የባንክ ውህደትና የተቋማት ግዢ እንዲሁም ካፒታልን የማሳደግ ውሳኔዎች የፋይናንስ ዘርፉ በተለያዩ ወቅቶችና ሁኔታዎች የተጠቀማቸው የለውጥ መሳሪያዎች ሆነው ታይተዋል ያሉት አቶ ደረጀ አንዳንድ ሀገራት የፋይናንስ ተቋማትን ጥንካሬ ለማሳደግና የገበያ ተወዳዳሪነትን ለማጠናከር አማራጮችን መጠቀማቸውን አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በውስጣዊ አቅማቸው ላይ ተመስርተው ተፈጥሯዊ እድገትን፤ የካፒታል ጭማሪን ወይም ሌሎች የመዋቅር ማሻሻያዎችን እንደመረጡ ተናግረዋል፡፡
የተመረጠው አቅጣጫ በእያንዳንዱ ሀገር የኢኮኖሚ ሁኔታ፣ የፋይናንስ ሥርዓት ባህሪ፤ የቁጥጥር ማዕቀፍና የገበያ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
እየጨመረ የመጣው የካፒታል አቅም መስፈርት ባንኮች የገንዘብ ጥንካሬያቸውን እንዲያሳድጉ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶችን እንዲደግፉና ከቀጣናዊና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በተሻለ ሁኔታ እንዲወዳደሩ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡
የካፒታል መጠን ብቻውን ግብ አይደለም ሲሉ የተናገሩት አቶ ደረጀ ዋናው ግብ ዓለም አቀፋዊ ፉክክርን የሚቋቋሙ፤ በቴክኖሎጂ የተደገፉ በአስተዳደር የጠነከሩና ለኢኮኖሚው ተጨባጭ እሴት የሚፈጥሩ የፋይናንስ ተቋማትን መገንባት እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡
በዘመን ባንክ የፋይናንስ ዘርፉ እድገት በውይይት፣ በትብብርና በጋራ እይታ የሚሳካ ነው ብሎ እንደሚያምን አስረድተዋል፡፡
በፓናል ውይይቱ ላይ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ ባንኮቻችን አዲሱን የካፒታል መስፈርት አንዴት ያሟላሉ? ውህደትና ግዥ ምን ዕድሎችንና ምን ተግዳሮቶችን ይዘው መጥተዋል? ከሌሎች ሀገራት ምን እንማራለን? ተቆጣጣሪዎች ባንኮች፤ ባለድርሻ አካላትና ባለ አክሲዮኖች በጋራ ምን መስራት አለባቸው? በሚሉ ጉዳዮችላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን ብሔራዊ ባንክ ለባንኮች የተከፈለ ካፒታል መጠን እንዲያሟሉ ያስቀመጠው ጊዜ ገደቡ መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡
የተወሰኑ ባንኮች በብሔራዊ ባንክ የተቀመጠውን የካፒታል መጠን ማሟላት እንዳልቻሉ ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ የባንኮች ምስረታ ከብሔርና ከሀይማኞት ጋር የተያያዙ እንደሆኑ አስታውሰው በመዋሀድ ጠንካራ ሆነው ለመውጣት ፈተና እንደሚገጥማቸው ጠቁመዋል፡፡
የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ ለመግባት ፍላጎት እየሳዩ እንደሚገኙ የተናገሩት ፕሮፌሰር አለማየሁ በተለይ ሀይማኖትን መሰረት ያደረጉ ባንኮች ከመካከለኝው ምስራቅ በሚመጡ ባንኮች ሊዋጡ ይችላሉ ሲሉ ስጋታቸውን አስቀምጠዋል፡፡@seco


