የግብርና ሚኒስቴር በአፍሪካ ልማት ባንክ ድጋፍና በ10.15 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ ዘመናዊ የዶሮ ጫጩት ማስፈልፈያ ተቋም ለመገንባት ከ”አግሪፋም” ኩባንያ ጋር ስምምነት ተፈራርሟል።
ስምምነቱ የኢትዮጵያን የዶሮ ምርት አቅም ለማሳደግ እና በአገር አቀፍ ደረጃ በዘርፉ ለተሰማሩ አርሶ አደሮች ጥራት ያለውን የምርት ግብዓት በተመጣጣኝ ዋጋ ለማዳረስ የተቀረጸው “የኢትዮጵያ የዶሮ እሴት ሰንሰለት ልማት ፕሮግራም” አካል መሆኑ ተጠቁሟል።
ፕሮጀክቱ በዓመት 63 ሚሊዮን እንቁላል የማሳቀፍ አቅም እንደሚኖረው የተገለጸ ሲሆን፣ በአገር ውስጥ ያለውን የዘመናዊ ጫጩት መፈልፈያ አቅም በእጅጉ እንደሚያሳድገው ይጠበቃል።
የውል ስምምነቱን በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) እና የአግሪፋም ኩባንያ ተወካይ ጃሪ ዣኦ ተፈራርመውታል። እንደ ስምምነቱ ከሆነ አግሪፋም ኩባንያ ግንባታውን በአንድ ሳምንት ውስጥ በመጀመር፣ በአስራ ሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ ተስማምቷል።
ይህ ተቋም ወደ ሥራ ሲገባ፣ የኢትዮጵያን የዶሮ ኢንዱስትሪ በማዘመን ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውና ለዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወሳኝ ድርሻ እንደሚኖረው በስነ-ስርዓቱ ወቅት ተገልጿል።@seco


