የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ (ESX) ሳምንታዊ የአክሲዮን (ኢኩዊቲ) የግብይት መጠኑን ለመጀመሪያ ጊዜ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ በማሻገር አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ ያስመዘገበ ሲሆን፣ ይህም በሀገሪቱ የካፒታል ገበያ ላይ እየገነባ የመጣውን የባለሀብቶች ከፍተኛ ተሳትፎ እና እምነት የሚያንጸባርቅ መሆኑ ተገልጿል።
የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ዋና ስራ አስፈፃሚ ጥላሁን እስማኤል ካሳሁን እንደገለጹት፣ ለኢትዮጵያ ወጣት የካፒታል ገበያ በአንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ ይህን ያህል የግብይት መጠን ማስመዝገብ መቻሉ የሚደነቅና ትልቅ መሻሻልን የሚያሳይ ነው።
ከሰኔ 8 እስከ 12 ቀን 2018 ዓ.ም በነበረው የገበያ አፈፃፀም መሠረት፣ በገበያው ላይ በዝርዝር በተካተቱት 4 ኩባንያዎች መካከል በተደረጉ 279 ግብይቶች በአጠቃላይ 350,111 አክሲዮኖች የተለዋወጡ ሲሆን፣ ይህም አጠቃላይ የግብይቱን ዋጋ 1.025 ቢሊዮን ብር አድርሶታል።
በተጨማሪም በባንኮች መካከል በሚደረገው የገንዘብ ገበያ የተከማቸው አጠቃላይ የግብይት መጠን 3.32 ትሪሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ በሳምንቱ ውስጥ የአንድ ቀን ግብይቶች በ12.416% የወለድ ተመን 66.3 ቢሊዮን ብር፣ የ7 ቀናት ግብይቶች ደግሞ በ15.634% የወለድ ተመን 49.8 ቢሊዮን ብር ሆነው ተመዝግበዋል።
ዋና ስራ አስፈፃሚው ጥላሁን አክለው እንደገለጹት፣ በሚቀጥለው ሳምንት ሌላ ተጨማሪ አዲስ ኩባንያ በይፋ በገበያው ላይ የሚመዘገብ በመሆኑ ለህዝብ ባለሀብቶች አዲስ የኢንቨስትመንት አማራጭ ይዞ ይመጣል። የሀገሪቱን የግል ዘርፍ ሰፊና ያልተነካ አቅም ያጎሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው፣ በቀጣዮቹ 1 እና 2 ዓመታት ውስጥ በሰነደ ሙዓለዋያት ገበያው ላይ የሚዘረዘሩትን ኩባንያዎች ቁጥር ከ50 እስከ 60 ለማድረስ ሙሉ እምነት እንዳላቸውና ለዚህም በትጋት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።@seco


