ገቢዎች ሚኒስቴር መሰብሰብ አልቻለም የተባለዉ ከ8.4 ቢሊዮን ብር በላይ የታክስ ዕዳ እንዲሰረዝ ተጠየቀ

የገቢዎች ሚኒስቴር በተለያዩ የሀገሪቱ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች ለረጅም ዓመታት ሳይሰበሰብ የቆየና ሙሉ በሙሉ ሊሰበስብ አልቻለም የተባለዉ እና ከ8.4 ቢሊዮን ብር በላይ የሚጠጋ የታክስ ዕዳ እንዲሰረዝ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ጠየቀ።

ይህ እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው ሊሰበሰብ የማይችል የታክስ ዕዳ በተቋሙ የሒሳብ መዛግብት ላይ ለረጅም ጊዜ ተከማችቶ መቆየቱ፣ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን ትክክለኛ የፋይናንስ አቋም እና የዕዳ አሰባሰብ ውጤታማነት በአሉታዊ መልኩ የሚያንጸባርቅ እንደሆነ ኢቢቪ የተመለከተችዉ ሪፖርት አመልክቷል።

ይህ በአስቸኳይ እንዲሰበሰብ ካልሆነ ግን እንዲሰረዝ ተብሎ የተጠየቀዉ የታክስ ዕዳ የተመዘገበው ከ2015 በጀት ዓመት ጀምሮ እስከ 2018 በጀት ዓመት አንደኛ ሩብ ዓመት ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ሲሆን፣ በተለያዩ ምክንያቶች ግብራቸውን ሳይከፍሉ በቆዩ፣ አድራሻቸውን ባቀያየሩ ወይም ሙሉ በሙሉ በጠፉ ግብር ከፋዮች ላይ የተከማቸ የቆየ የመንግሥት ውዝፍ የገቢ ድርሻ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

ይህንን በቢሊዮኖች የሚቆጠር ከፍተኛ የፋይናንስ ዕዳ ከስምሪት መዝገብ ላይ ለመሰረዝ ወይም ሕጋዊ እልባት ለመስጠት እንዲቻል፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ያሉትን ተጨባጭ ማረጋገጫዎች በማደራጀትና ከሚመለከታቸው የሕግና የፋይናንስ አካላት ጋር በመተባበር በአስቸኳይ ውሳኔ እንዲያገኝ እና ማሻሻያ እንዲደረግበት በኦዲት ሪፖርቱ ተጠይቋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር በገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ኦዲት አሠራር ሥርዓት ላይ ያከናወነውን ዝርዝር የክዋኔ ኦዲት እንደሚያመለክተውከታክስ ዕዳ አሰባሰብ ላይ በተጨማሪም፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀምና በመረጃ ልውውጥ ረገድም ሰፊ ክፍተቶች እንዳሉበት አጋልጧል፡፡

እንደ ሪፖርቱ ከሆነ የታክስ መረጃ ድጋፍ አገልግሎትእና የኤሌክትሮኒክስ ግብር ማሳወቂያ ሥርዓቶች ባለመተሳሰራቸው ምክንያት በመካከላቸው የመረጃ አለመናበብ ችግር እንዳለ ተጋልጧል፡ ከዚህም በላይ ከ2015 እስከ 2018 በጀት ዓመት 1ኛ ሩብ ዓመት ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የ9,497 የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎች ያሉበት ሁኔታና አድራሻ የማይታወቅ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ መሣሪያዎቹን በጂፒኤስ ለመቆጣጠር የሚያስችል ሥርዓት ባለመኖሩ ግብር ከፋዮች መሣሪያዎቹን ይዘው የሚሰወሩበት ሁኔታ መፈጠሩ በጥናቱ ተመልክቷል፡፡

ከከፍተኛው ሊሰበሰብ የማይችል የታክስ ዕዳ በተጨማሪ፣ የዋጋ ትልልፍ ግብይት ቁጥጥር ማነስ ሌላው ተቋማዊ ክፍተት ሆኖ መገኘቱ ተገልጿል፡፡ ኢትዮጵያ አባል ከሆኑባቸው ዓለም አቀፍ የንግድ ተቋማት ጋር በተያያዘ፣ ከሀገር ውጭ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት ያላቸው ድርጅቶች የሚያደርጉት የዋጋ ትልልፍ ግብይት የሚሸጥበት ዋጋ የማይታወቅ መሆኑም ተጠቁሟል።

እንዲሁም የድርጅቶች ልዩ ልዩ ወጪዎች (ለምሳሌ የወለድ፣ የእርጅና ቅናሽ፣ የደሞዝ፣ የነዳጅ፣ የጥገና፣ የማስታወቂያ፣ የትራንስፖርት እና የአበል ወጪዎች) በሌጀር ላይ በግልጽ ባለመቀመጣቸው ምክንያት በግብር ከፋዮች ዘንድ የቅሬታ መበራከት ምክንያት መሆኑ ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡SECO

Related

አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ እና ከፍተኛ የመንግስት የስራ  ሀላፊዎች ከኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ሀላፊነታቸው ተነሱ

ድርጅቱን በቦርድ ሊቀመንበርነት ሲመሩት የነበሩት አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ፣ምክትል  ሰብሳቢ...

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የተሰጠው የእገዳ መመሪያ ውዝግብ አስነሳ​​

በኢትዮጵያ የሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) እና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ...

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች የሦስት እርከን የደመወዝ ጭማሪ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ጸደቀ

የሀገሪቱ ግዙፉ መንግሥታዊ የፋይናንስ ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ...

አዳማ  የፈጣን ስማርት የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ መሙያ  ተጠቃሚ  ሆነች

በአለምሰገድ እስጢፋኖስ ኢትዮ ቴሌኮም በዛሬው ዕለት ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዲስ አበባ...

የኢትዮጵያ የሚዲያ ልህቀት ማዕከል ተመረቀ

“ከማገዳችን በፊት ከአምስቴ በላይ ማስጠንቀቂያ ሰጥተናል!” የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ያስመረቀው...

Popular Categories