አማራ ባንክ እንዳስታወቀው የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ዝርዝር መስፈርቶችን በማስቀመጥ በከፍተኛ ጥንቃቄ እና የኃላፊነት ስሜት እጩዎችን በመለየት ሲገመግም ቆይቶ አቶ ይህንዓለም አቅናውን በትምህርት ዝግጅታቻው፣ በባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ ለበርካታ ዓመታት በከፍተኛ ኃላፊነት ያካበቱትን ልምድ እና ስትራቲጂያዊ የአመራር ብቃት ከግመት በማስገባት የአማራ ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አድርጎ ሾሟል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክም ሹመታቸውን በዛሬው ዕለት እንዳጸደቀ ነው የተገለጸው፡፡
የአማራ ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው የተሾሙት አቶ ይህንዓለም አቅናው በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከ25 ዓመታት በላይ የሥራ ልምድ እንዳላቸው ተጠቁሟል፡፡
አዲሱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የንግድና ኢኮኖሚክስ ፋኩልቲ በሂሳብ አያያዝ የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም በኢንፎርሜሽን ሲስተምስ በ2005 (እ.ኤ.አ) ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። ከዚህም በተጨማሪ በለንደን፣ ዩናይትድ ኪንግደም ከሚገኘው የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ማህበር (Association of Chartered Certified Accountants – ACCA) የላቀ የሙያ ማረጋገጫ በ2013 (እ.ኤ.አ) አግኝተዋል፡፡
እንዲሁም በ2014 (እ.ኤ.አ) ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ድህረ-ምረቃ ትምህርት ቤት በሥራ አመራር የማስተርስ ዲግሪያቸውን (Executive MBA) ማግኘት ችለዋል።
አቶ ይህንዓለም ከ25 ዓመታት በላይ የዘለቀ የሥራ ዘመናቸውን ከኢትዮጵያ ቀዳሚና ግዙፍ የግል ባንኮች አንዱ በሆነው ዳሸን ባንክ ውስጥ ያሳለፉ ሲሆን፣ ከጀማሪ ባለሙያነት እስከ ከፍተኛ የአመራር እርከን ድረስ በተለያዩ ኃላፊነቶች አገልግለዋል።seco


