ደካማ ድህረ ምርት እና ሎጅስቲክ ለሙዝ ወጪ ንግድ እንቅፋት መሆናቸው ተገለጸ

በኢትዮጵያ የሚመረተው ዓለም አቀፍ ደረጃ ያሟላ ሙዝ ለውጭ ገበያ ሊቀርብ እንዳልቻለ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

የተቋሙ የሰብል ምርምር ዳይሬክተር ዶክተር ፈቃዱ ጉርሙ እንዳሉት ኢንስቲትዩቱ የዓለምን የጥራት መስፈርት የጠበቀ የሙዝ ዝርያ አጎልምሶ ለአርሶ አደሮች አሰራጭቷል።

የዚህ ዝርያ ውጤት ለተለያዩ ሃገራት ገበያ ቢቀርብ የተፈላጊነት ችግር አይገጥመውም ሲል ነው ተቋሙ ያስታወቀው።

ሆኖም ከማሳ ዝግጅት እስከ ምርት ስብሰባና ማጓጓዣ ድረስ ያለው ሂደት ጥንቃቄ ስለሚጎድለው የኢትዮጵያን ሙዝ እንዳይፈለግ አድርጎታል።

ከዚያም ባለፈ የሚለማው ሙዝ መጠን ዝቅተኛ በመሆኑ የሃገር ውስጡን ፍጆታ አርክቶ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ አልተቻለም።

ኢትዮጵያ የምትገኝበት መልከዐ ምድር ሙዝ በከፍተኛ መጠን ለሚፈለግበት መካከለኛው ምስራቅና አውሮፓ ቀጠና ለመላክ ያላትን ዕድል እንዳልተጠቀመችበት ነው ዶክተር ፈቃዱ የገለፁት።

በሙዝ እሴት ወደ ስኬት በሚል ርዕስ ባሳለፍነው ሐሙስ በአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል፣ በፍራፍሬ የእሴት ሰንሰለት የሚሳተፉ አካላትን ያሰባሰበ ጉባዔ በኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራች ላኪዎች ማኅበር አዘጋጅነት ተካሂዷል።

የማኅበሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ዘውዴ ጉባዔው ኢትዮጵያን በዓለም የሙዝ እሴት ሰንሰለት ውስጥ የሚያሳትፍ ሃሳብ እንዲያመነጭ የታለመ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የሙዝ ልማት አሁን የሚገኝበት ይዞታ፣ የዓለም አቀፉ ገበያ አዝማሚያ፣ የአቅርቦት ሰንሰለትና በድህረ ምርት አያያዝ ላይ የሚፈጠረው የጥንቃቄ ችግር ውይይት ተደርጎበታል።

የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራች ላኪዎች ማኅበር የምርትን ጥራት ለማሻሻል፣ መጠኑን ለማሳደግ፣ እንዲሁም አቅርቦትን ከፍላጎት ጋር ለማጣጣም መድረኩን እንደ ወሳኝ የመሸጋገሪያ ምዕራፍ ሊጠቀምበት እንዳለመ ነው አቶ ቴዎድሮስ ያስታወቁት።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ መጠን ያለው ሙዝ የምታለማው ህንድ ብትሆንም አብዛኛውን ለሀገር ውስጥ ገበያ ነው የምታውለው።

የላቲን አሜሪካዋ ሃገር ኢኳዶር እስከ መካከለኛው ምስራቅና አውሮፓ በመላክ ቀዳሚ ነች።

ኢትዮጵያ ይህንን የገበያ ዕድል ልትጠቀምበት እንደምትችል ነው በጉባኤው ላይ የተነሳው።

በዓለም ከሚለማው ሃምሣ ሚሊዮን ቶን ሙዝ ውስጥ ሁለት ሶስተኛው ለሌሎች ሃገራት ይሸጣል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ከ250 ሺህ ሄክታር የበለጠ መሬት በተሻሻለ የሙዝ ዝርያ ተሸፍኗል።

በ2018  በጀት አመት ከሰባ ሶስት ሚሊየን ኩንታል በላይ ሙዝ ተሰብስቧል።

በሒልተኑ ጉባዔ ስለ ኢትዮጵያ እምቅ የሙዝ ልማት አቅም የተወያዩት ከሁለት መቶ በላይ የአትክልትና ፍራፍሬ አዋቂዎች፣ አምራች ላኪዎች፣ የኅብረት ስራ ማኅበራት፣ የገንዘብ፣ የትምህርትና የምርምር ተቋማት፣ እንዲሁም የልማት አጋር የተባሉ ድርጅቶች ተወካዮች ናቸው።

ሙዝ መንግስት የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬውን ዘርፍ ለማሳደግ የነደፈው የአስር ዓመት መሪ ዕቅድ አካል ነው።

የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራች ላኪዎች ማኅበርም ሙዝ ለሚያስገኘው ሰፊ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አስተዋፅዖ ለማድረግ እየሰራ ነው።SECO

Related

አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ እና ከፍተኛ የመንግስት የስራ  ሀላፊዎች ከኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ሀላፊነታቸው ተነሱ

ድርጅቱን በቦርድ ሊቀመንበርነት ሲመሩት የነበሩት አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ፣ምክትል  ሰብሳቢ...

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 220 ቦታዎች የሊዝ ጨረታ አወጣ

​የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ በዘጠኝ ክፍለ...

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የተሰጠው የእገዳ መመሪያ ውዝግብ አስነሳ​​

በኢትዮጵያ የሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) እና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ...

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች የሦስት እርከን የደመወዝ ጭማሪ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ጸደቀ

የሀገሪቱ ግዙፉ መንግሥታዊ የፋይናንስ ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ...

አዳማ  የፈጣን ስማርት የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ መሙያ  ተጠቃሚ  ሆነች

በአለምሰገድ እስጢፋኖስ ኢትዮ ቴሌኮም በዛሬው ዕለት ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዲስ አበባ...

Popular Categories