ጷጉሜ አብ የተሰኘ ኩባንያ አከናወንኩት ያለውን ጥናት መሰረት አድርጎ እንደገለጸው አስራ ሶስተኛው ወር ሰራተኞች ለአገልግሎታቸው ምንም ዓይነት ክፍያ አለማግኘታቸው የስራ ተነሳሽነታቸው ላይ ጫለው ብሏል፡፡
የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ኃይለአብ መረሳ እንደሚናገሩት ወርሃዊ ደሞዝ የሚታሰብላቸው ሰራተኞች በጷጉሜ ወር በስራ ገበታቸው ላይ ቢገኙ እንኳ ደሞዝ ስለማይታሰብላቸው ውጤታማ አፈጻጸም አያሳዩም፡፡
በመሆኑም ኢኮኖሚ ላይ ጫና እንዳለው ነው የተነገረው፡፡
ይህን ሁኔታ ለመቀየር በሃገር አቀፍ ደረጃ ፌስቲቫል ቢካሄድ የተሻለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መፍጠር እንደሚቻል ነው አቶ ኃይለ አብ የሚገልጹት፡፡
ድርጅታቸው በ2018 ወርሃ ጷጉሜ አምስቱንም ቀናት በተለያየ ሁነት ለማሳለፍ ተዘጋጅቷል፡፡
በተለይ ከጷጉሜ ሁለት ጀምሮ በአፍሪካ ህብረት ቅጽር ጊቢ ውስጥ ጷጉሜ ወርቃማ ወር በሚል መሪ ቃል የኢትዮጵያን ማኅበረሰባዊ ባህልና አኗኗር የሚገልጽ ትርዒት ይካሄዳል፡፡
ኢትዮጵያ ያላት የተፈጥሮ መስህብና የኢንቨስትመንት አማራጭ ይተዋወቃል፡፡
ከሁሉም የአፍሪካ ሃገራት የባህል ቡድኖች መጥተው ትርዒት እንዲያሳዩም ተጋብዘዋል፡፡
አቶ ኃይለአብ መረሳ የዘንድሮው ፌስቲቫል ጷጉሜ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት ዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ የሚያነሳሳ ስራ ይከናወናል ባይ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ በቀን መቁጠሪያዋ ላይ 13 ወራት ያላት ብቸኛ ሃገር እንደሆነች ማስተዋወቅም ትኩረት ይሰጠዋል፡፡
የጷጉሜ አብ ወሩን በፌስቲቫል ማክበር የጀመረው በ2008 የአዕምሮ ንብረት ባለቤትነት መብት ከወሰደ ወዲህ ነው፡፡ የዘንድሮው ዝግጅት ዘጠነኛ ዙር ይሆናል፡፡
ፌስቲቫሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ቅጽር ጊቢ የሚከናወነውም ጷጉሜን በአህጉሪቱና በዐለም አቀፍ ደረጃ ለማተዋወቅ ያግዛል በሚል እምነት ነው፡፡
ፌስቲቫሉ የሚካሄደው በሃገራችን በየአካባቢው ያለውን የአዲስ ዓመት አከባበር በሚያንጸባርቅ መልኩ ይሆናል፡፡
አመጋገብ፣ አለባበስ፣ የየብሄሩ የውዝዋዜና አጨፋፈር ስልት፣ እንዲሁም ሙዚቃ ይቀርባል፡፡
የፓናል ውይይትም እንደሚከናወን ይጠበቃል፡፡
የልጆች የዝናብ ላይ የጎዳና ሩጫም ይኖራል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች ዘንድ በጷጉሜ ወር ሶስተኛ ቀን በሩፋዔል ዐመታዊ በዐል የዝናብ ጥምቀት ላይ የሚታየው ስርዐት እንደሚከናወን ነው አቶ ኃይለአብ የተናገሩት፡፡
ፌስቲቫሉ አፍሪካዊያን የሚነጋገዱበትን ገበያ ለመፍጠር ያለመ ባዛርም ያካትታል፡፡
የቁንጅና ውድድርም የዝግጅቱ አካል ነው፡፡
እንደ ዋና ስራ አስፈጻሚው አባባል ፌስቲቫሉ ኢትዮጵያዊያንን እርስ በእርስና ከአፍሪካዊያን ጋር ለማስተዋወቅ ዕድል ይፈጥራል፡፡
አህጉራዊ አንድነትም ይንጸባረቅበታል፡፡SECO


