የውርስ ክርክር እና ቅሌት!

ሺ ብታረጅ ልጅ ያቦካው የሚባለው ተረት በድሜ ለገፋም ልጅ ልጅ ነው የሚያስብልህ ብዙ ክስተት አለ! አንብበው።

-10ሺ ብር ከንጉሱ ተሸልሟል!

-ስሙን D’Afrque Hotel በሉት አሉ በፈረንሳይኛ አፋቸውን እንደፈቱ የሚታሙት አፄ!

ያኔ አፄው የአፍሪካ አገራት አባቶችን ጋብዘው ህብረት እንጂ ለምን መለያየት ብለው ሊጠሩ ሲሉ እንግዶች ለማሳረፍ የሚሆን ቦታ ጭንቅ ሆነ።

ጊዎን ቢኖርም እጥረት እንደሚፈጠር ታውቋል እና ኢትዮጵያ ሆቴል ተገነባ።

በስምንት ወራት ሩጫ ደረሰ ለ1955 ዓም የግንቦቱ ታሪካዊ ስብሰባ።

ቀደም ሲል የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽንን በ5 ሚሊየን ብር አስገንብታ ለተባበሩት መንግስታት አበርክታ የአህጉሪቱ የዲፕሎማሲ መዲና መሆን የጀመረችው አዲስባ፤

እነ ጊዎን፣ ራስ እና ኢትዮጵያ ሆቴሎች አድባር የነበሩ ጊዜ እጥረቱን ለማቃለል ተጨማሪ ቅንጡ ሆኖ ወደ ስራ ገባ።

ተብሎለታል ዲ አፍሪክ ሆቴል በጥልያን ወረራ ባለውለታዋ በተሰየመው ሞክሲኮ አደባባይ ተገንብቶ ወደ ስራ ሲመጣ።

በ1958 (እኤአ በ1966) ግድም ንጉሱ ሲመርቁት “10 ሺ ብር ለአልሚው ሸለሙት፣” አሉኝ ታሪኩን የሚያውቁ።

እንደ መነሻ፤ ስራ ማእኬጃ ባለሀብቱ ሰይፉን አበጀህ ሊሉ ሌሎች አልሚዎችን ደግሞ ሊያነቃቁ።

እንደ እነ ማልኮም ኤክስ #MalcolmX አይነት ሲአይኤን (#CIA) ያንቀጠቀጡ የመብት ተሟጋቾች እና ስመ ጥር ዲፕሎማቶች እንዲሁ ሰሌብሪቲዎች በዛ ዘመን ኢትዮጵያን ሲጎበኙ በልበ ሙሉነት ለማስተናገድ ትልቅ አማራጭ የሆነ፡፡

ዛሬም ከነ ግርማ ሞገሱ በተንጣለለ ግቢ የሚገኘው ባለ ስድስት ወለሉ ሆቴል መጠሪያ ነው የሰፈሩ።

ንጉሱ መጠርያውን ሆቴል ዲ አፍሪክ አሉት።

በስጦታ ከቆዳ የተሰራ የአፍሪካ ካርታ ሰጡ የአፍሪካው አባት ለግርግዳ ማስዋቢያ።

ደሴቲቷም አልቀረች ብሎ ፈገግ አሰኘኝ ሆቴሉ ውስጥ ስንስተናገድ ስጦታውን ያየ ወዳጄ የ ማደጋካስካርን ፈንጠር ብሎ የተለጠፈ የቆዳ ቅርፅ እያሳየኝ።

ምነው ደሴት ብትሆንም ለውርስ የመጣ ደመኛ አረካትሳ እሷም እኮ የአፍሪካ አካል ነች ልለው አስቤ ቀልዱን ማፍዘዝ እንዳይሆን ብዬ ተውኩት።

የግል ቢሆንም እንደ ገፅታ ግንባታ እና እንግዶች እርካታ ስራው እንዲሰፋ ይፈልጉ ነበርና ይከታተሉት ነበር ይላሉ ስለሆቴሉ የሚያውቁ ጃንሆይን እያነሱ።

ታድያ ልክ እንደዛን ጊዜዋ ካፒታሊስቷ አዲስ አበባ ስራው ሞቀ!

በዝነኛ የምሽት ክበቡ እነ አስቴር አወቀን ይዞ ታወቀ።

ዛሬ ግን ታሪክ ተቀየረ!

ሲያልቅ አያምር ነው መሰል ነገሩ።

የዚህ ግዙፍ ታሪክ ባለቤት እና ምርጥ ንግድ መስራች የሆኑት አርቆ አሳቢው አቶ ሰይፉ ገብረዮሃንስ ወራሾች ንብረታቸውን ከመንግስት ገፈፋ በኋላ መልሰው እጃቸው ቢያስገቡም የውርስ ነገር አደባባይ ይዟቸው ከመውጣት አልፎ ክፍፍሉ ላይ ሲተራመሱ ሲታይ አወይ የጊዜ ነገር አስባለ።

የባለሃብቱ የበኩር ልጅ ብስራት ሰይፉ ንብረቱን እኔ እንድወርስ ነው አባቴ የተናዘዘው ሲሉ ነበር የተነሱት።

በርግጥ ንብረቱን ከመንግስት ውርስ በማስመለስ ሂደት መልካም ሰርተዋል። ልክ ናቸው እንደ በኩር ንብረት ማስመለስ ተገቢ ሃላፊነት ነው።

ይሁን እና ሌሎች የጋብቻ እና ውላጅ ዘመዶች ደግሞ ተው እንጂ…. እኛም የአባታችን/የትዳር አጋር ድረሻ ይገባናል በማለታቸው ለአመታት ተከራከሩ።

ለዚያውም በእልህ!

በኢትዮጵያ ፍርድ ቤት ጉዳይ ከምትጨርስ አዲስ ስራ ቀይስ! ቢባልም ሲከራከሩ፣ ሲከራከሩ፣ ሲኖሩ፣ ሲኖሩ ቆዩ፤

ፍርድ ተሰጠ ከ20 አመታት በኋላ።

ከዚህ ጊዜ በኋላ፣ ቀላል የማይባሉ ወራሾች ሳይበሉት ተተኩ በሌላ፣

ብዙዎች ተወልደው እና ደርሰው የውርስ ጓጊ ከሆኑ በኋላ፤

የተሰጠው ፍርድ “ማን ፍርድ ቤት ድርሽ በሉ አላችሁ” የሚያሰኝ ነው ተባለ።

“እዛው ተስማምታችይሁ አትጨርሱም ነበር!” አሉ ተቺዎች።

“ተራ ቤት በሚያወጣበት ዋጋ ይሸጥ ነው ያለው! “ሲሉ አሟሟቁ ደላሎች።

“ቦታው እምብርት ነው ካሬውስ ብትሉ፣” ሲሉ አከሉ የፍርድ ቤትን ግምት የታዘቡ ዋጋ አውጭዎች።

በሰላም መካፈል እንዴት ሲደረግ አባቴ ይሄን ንብረት ለኔ ነው የሰጠው ቀሪውን ሃብት ይካፈሉ፣ አይ ያማ አይሆንም ከዚህም የባሌ፣ የአባቴ እና አያቴ ድርሻ ይድረሰን ብለው ሲጓተቱ የነበሩ ዘመዳሞች አቤት እንበል አሉ ዛሬ ተስማሙ።

ቀኝ ኋላ ዙር! ይልሃል ይሄኔ ነው።

የሆነው ሁኗል ዜናው ሲዘገብ ቆይቷል።

የዚህን መጨረሻ ዘገባ የሰራው እና ለኔ ወግ መነሻ የሆነው የፎርቹን ጋዜጠኛ ያኔ ክሱ ሲጠነሰስ ምናልባት አልተወለደ ወይ የኬጂ ተማሪ ይሆን ይሆናል።

ብቻ ወራሽ ከዚህ ካልተማረ ከምን ሊማር ይችላል።

በርግጥ እልህ አለምን ሲንጥ አይተናል።

የቤተሰብ ፀብ ደግሞ ሲግም ጣጣው አያድርስ መሆኑን በታሪክ ሆነ ሀይማኖት ትርክት ብዙ ተምረናል ግን ያው እዛ ሲሆን እየተገረምን እዚህ ደርሰናል።

እዚሁ ከተማ ብዙዎች ለትልቅ ሀብት ውርስ ሲፋለሙ በገዛ ሀብታቸው ደሃ ሆነው አይተናል።

የታዋቂ እና የአገር ባለውለታ ልጆች ሰው ጉድ እስኪል ሲናከሱ ታዝበናል።

የኛ አገር የፍርድ ቤት ጉዞ እና ሂደትም እጅግ ይበዛል።

እውነቴን ነው!

ንብረት በ184 ሚሊየን ብር ሸጣችሁ ተካፈሉ ለማለት እንዴት 20 አመት ይፈጃል!

ነግደን ስለማናቅ ለነገሩ የት ይገባናል።

በሙግት እና ፋይል በማገላበጥ እንደዋዛ ዘመናት ይፈጃል።

ለዚህ ነው የመንግስት ቢሮክራሲ ውስጥ ያለ ሰው ንግድ ይኑረው ወይ በግል ዘርፍ ስራ ሊያልፍ ይገባል የሚባለው፡፡

አለያ የት ያቅልሃል ቢሮ ቁጥር 3 ጠይቅ ይልሃል፣
ለዚህ ጉዳይ ከ 8 ወር በኋላ ተመለስ፣ መመሪያ አይፈቅድም፣ እንደዛ፣ እንደዚህ እያለ ልብህን ዝቅ ያደርገዋል።

ያንተ ስራ መች ይገባዋል። በአንድ ቃል ተካፈሉ ለማለት 20 አመት ያመላልስሃል።

በመሃል ስንት ቢዝነስ ያመልጥሃል።

ምርጥ የሽቀላ season አሳልፎብህ ከብዙ የፍርድ ጉዞ በኋላ ለይግባኝ ፋይል በማገላበጥ ጊዜ ያስጠፋሃል።

ያዙኝ ልቀቁኝ ያስባለህ እልህ ይበርድ እና ኸረ ይቅርብኝ ከነ ድህነቴ አርፌ ልቀመጥ ሊያስብልህ ይችላል።

በርግጥ ነገሩ ሲያዝግህ እና እድል ገጥሞህ ወደ ቀልብህ ከተመለስክ ከተናከስከው ወንድምህ ጋር ይቅር የመባባል እድል ሊፈጥርልህ ይችላል።

በርግጥ በውርስ ጉዳይ ከሆነ በየትኛውም ወገን እና የመውረስ ደረጃ ተቀመጥ ቀድመህ ካልነቃህ “አርፈህ አትስማማም ይበልህ” ነው የሚልህ በልቡ አጠገብህ ያለው ሁሉ።

ይናደድብሃል!

በዲ አፍሪክ ጉዳይ ግዙፍ ህንፃ ይዞ፣ 3 ሺ 800 ካሬ ሜትር በአዲስአባ እምብርት ታቅፎ፣ 20 አመት ለውርስ ተመላልሶ የሀራጅ ግምቱ የሆነ ቪላ ቤት ዋጋ ነው ሲባል ምን ይሰማሃል።

ይሄ ንብረት ተሸጦ የሚደርስህ ገንዘብ 100 ካሬ ኮንዶምኒየም እንደማይገዛልህ ሲገባህ ነው ምነው ሁሉም ቀርቶ ያኔ በ90ዎቹ በሰላም በተካፈልኩ የምትለው።

የሚያሳዝነው ይሄን የሚያነብ አዲስ ወራሽ አለመማሩ፤ የገዛ ንብረቱን ሰው ያካፍለኝ ብሎ አሳልፎ ሰጥቶ 20 አመት ፍርድ ቤት እየተመላለሰ ውሳኔ መጠበቁ ነው።

ነገሩ ከ20 አመት እንደሚሻገር ልቡ ይነግረዋል፡፡

ግን ድርቅ፣ ግግም ይላል።

“የኛስ ይለያል!” ያለው ማን ነበር!

ይኸው የዲ አፍሪክ ወራሾች እንሽጥ እና እንብላ የሚለው ጉዳይ ሌላ ዳገት ሆኖባቸዋል። ግምቱ አንሷል ሲሉ ቅሬታ አስገብተዋል።

“ሃራጅ ከወጣ በኋላ ፍርድ ቤት ይሰማቸዋል?” ሲል ጠይቋል አንዱ የሃራጅ ኤክስፐርት።

“1 ቢሊየን ሲያንሰው ነው፣” ብለው አሟሙቀዋቸዋል ገማቾች፡፡

የዛሬ 30 አመት ብትነቃ ኖሮ ዛሬ ስንት ዲ አፍሪክ ከፍተህ ነበር ይልሃል አሽሟጣጭ።

ጨዋታው ላይ 10 አመት ጨምሮበት።

ግን ምን ያደርጋል አዲስ ወራሽ ከዚህ አይማርም ይልሃል ጨምሮ።

መንግስት ግን ቢያንስ ለዚህ አይነት ጉዳይ ሂደቱን ፈጠን አርገው እንጂ?

በቤተሰብ ፀብ መካከል የተጎዳው የአገር ኢኮኖሚ እኮ ነው።

ለነገሩ ከግል ዘርፍ ካልመጣህ ካፒታልስትነት እንዴት ይገባሃል።

ይሄ ንብረት ባለፉት በርካታ አመታት ተረጋግቶ ሰርቶ ቢሆን ያ የያኔ ዝናው ተጠብቆ በልጅ፣ የልጅ ልጅ ተባርኮ እና አድጎ ቢሆን ለስንት ሰው እንጀራ ወጥቶ ነበር፡፡

ስንት ሰው ተዝናንቶ፣ ስንት ግብር ገብቶ ነበር!

የወራሾች አጭር ታሪክ

እራሱ ፈቅዶ እና ወዶ አደባባይ ያወጣው የወራሽ ታሪክ ይኸውልህ።

ብስራት ሰይፉ አባቴ ሆቴሉን በኑዛዜ ቃል አውርሶኛል ሰሜን ማዘጋጃ ያለው ንብረት ነው የሌሎቹ ውርስ ሲል ቢከራከርም፤

የሰይፉ የትዳር አጋር እና ሁለት ልጅ ከሰይፉ እንዲሁም ሁለት ከሌላ ያፈሩ አማረች ይገዙ የሆቴሉ ግማሽ ለኔ ነው ሲሉ አቤት ብለዋል።

ጌታቸው ሰይፉ ደግሞ ከሌላ ተወልዶ ለውርስ መዘጋጀቱ ታውቋል።

አማረች ማለፋቸውን ተከትሎ የውርስ ትግሉ ወደ 4 ልጆቻቸው(በለጥሻቸው፣ ምህረት፣ አለማየሁ እና ታምሩ) ይወርዳል።

ታዲዎስ እና ምስራቅን ጨምሮ የባለሀብቱ ሰይፉ 3 የልጅ ልጆች አባታቸው ጌታቸው ሲሞቱ የአያታቸውን ሀብት ሊካፈሉ ለአመታት ጉዳዩን በፍርድ ቤት ውጣ ውረድ ተከታትለዋል።

ሰበር ፍርድ ቤት እኩል ተካፈሉ ሲል በስተመጨረሻ ወስኗል።(አሁን ለዚህ ሰበር ድረስ ሂኬዳል?)

ልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ደግሞ በሃራጅ ሲሸጥ መነሻው 184 ሚሊየን ብር ይሁን ሲል የንብረት ግምት አውጥቷል፡፡

ይሄ ደግሞ ወራሾችን እርር ድብን አድርጓል፡፡ (ንብረትህን አሳልፈህ ሰጥተህ የምን መበሳጨት ነው? ይልሃል የዚህ ወግ አንባቢ)

እኔ እንዲሸጥ አልፈልግም ስታገል የኖርኩት ለዚሁ ነው ይባባሉልሃል ባለቀ ሰአት፡፡

በሃራጁ ተሳትፈን የአባታችንን እና እናታችንን ንብረት ማስከበር አለብን ብለዋል የአማረች ልጆች፡፡

የኛስ ይለያል!

ተካሳሽ ንቃ መዋለድ የትም ያለ ነው መስመር የያዘ ድርጅት ግን 100 አመታትን ሲሻገር እንኳን ቤተሰብ ዘር ማንዘርን ሲያበለፅግ ነው የታየው በሌላ አገር።

Related

የወደብ ባለቤትነት ምንነት

ሙሉቀን የወንድወሰን (ነፃ ሃሳብ) ለኢኮኖሚ ወደብ ምን ማለት እንደሆነ እንዲገባህ...

የሰላም ፣ የፍቅር እና የትውልድ ጥሪ

ለውድ የኢትዮጵያ ህዝብ ለተከበራችሁ የመንግስትና የፖለቲካ መሪዎች ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሀገራችን...

Popular Categories