አስቸኳይ ብሎ የሶማሌ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያወጣው መግለጫ እንደገለፀው የአሜሪካ ኤምባሲ ዶሎ ዞንን በተመለከተ ያወጣው የጉዞ ማስጠንቀቂያ በአካባቢው ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ አያንጸባርቅም ብሎታል፡፡
በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ሴፕቴምበር 16/2026 ዶሎ ዞንን በተመለከተ ያወጣውን የጉዞ ማስጠንቀቂያ ተመልክቷል ያለው የክልሉ ቢሮ መግለጫ።
ኤምባሲው ያወጣው ማስታወቂያ በችኮላ የወጣና በዶሎ ዞን ያለውን ተጨባጭ የሰላምና የደኅንነት ሁኔታ በትክክል የማያንጸባርቅ ፤ በአካባቢው ያለውን ሁኔታ በየጊዜው ከሚከታተሉት የክልሉ አስተዳደር የደህንነትና ፀጥታ ተቋማት ጋር በቂ የመረጃ ማጣራትና ምክክር ሳይደረግበት የወጣ ነው ብሏል።
አክሎም የክልሉ አስተዳደርና የፀጥታ ተቋማት ባረጋገጡት መሠረት፣ ዞኑ ሰላማዊና የተረጋጋ ነው።
የመንግሥት ተቋማትም መደበኛ ኃላፊነታቸውን በሙሉ እየተወጡ ሲሆን፣ የሰው፣ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ፣ የንግድ ሥራዎች፣ የማኅበራዊ አገልግሎቶችና ሌሎች ዕለታዊ ተግባራት በመደበኛነት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብሏል ከደቂቃዎች በፊት የወጣው መግለጫ።
የሶማሌ ክልል መንግሥት ለነዋሪዎች፣ ለእንግዶችና በክልሉ ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ደኅንነት ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል ሲል ነው ያከለው።
ልዩ ጥንቃቄ የሚያስፈልግ የፀጥታ ሁኔታ ካጋጠመም፣ የሚመለከታቸው ተቋማት ትክክለኛ፣ ወቅታዊና ይፋዊ መረጃ ለሕዝቡ ያደርሳሉ ብሎ አክሎ።
የዲፕሎማሲ ተቋማትና የጉዞ ማስጠንቀቂያዎችን የሚያወጡ ሌሎች አካላት መረጃዎችን ከማሰራጨታቸው በፊት መሬት ላይ ያሉ እውነታዎችን በአግባቡ እንዲያጣሩና ከሶማሌ ክልል የሚመለከታቸው ተቋማት ጋር እንዲመካከሩ ነው ጥሪ ያቀረበው።SECO


