2ኛው የኢትዮጵያ አለም አቀፍ የቴምር ፌስቲቫል በአፋር ክልል ሊካሄድ ነው።
በአለምሰገድ እስጢፋኖስ
ኢትዮጵያ ለቴምር ልማት ተስማሚ የሆነ የአየር ጠባይ እና የመሬት ሀብት እንዳላትና በተለይም በአፋር፣ በሶማሌ፣ በድሬዳዋ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በታችኛው ኦሞ ሸለቆ ያሉ ዝቅተኛ እና ቆላማ አካባቢዎች ለቴምር ዛፍ እድገትና ምርታማነት ተስማሚ እንደሆኑ በጥናት መረጋገጡ ነው የተነገረው።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ፕሮፌሰር አሊ መሀመድ ዛሬ በሰጡት መግለጫ 2ኛው የኢትዮጵያ አለም አቀፍ የቴምር ፌስቲቫል ከመስከረም 10 እሰከ 12 በአፋር ክልል ይካሄዳል፡፡
ሀገሪቱ ከ5000 ሺህ እስከ 700 ሺህ ሄክታር መሬት ማልማት የሚያስችል አቅም ቢኖራትም በአሁኑ ወቅት እየለማ ያለው 6 ሺህ ሄክታር ብቻ እንደሆነ ነው የተናገሩት።
ይህም ማልማት ከሚቻለው መሬት 1 ነጥብ 2 በመቶ ብቻ እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡ በዚህ ምክንያት በቴምር ተገቢውን ምርት እየተገኘ አይደለም ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የቴምር ምርትን በማስፋት ተገቢውን ምርት ለማግኘት የ10 አመት ስትራቴጂ ተነድፎ ወደ ስራ መገባቱን ነው የገለጹት፡፡
በኢትዮጵየያ ቴምር የሚያመርቱ አካባቢዎችን በጥናት የተለየ ሲሆን ዝርያ በማባዛት የማሰራጨት ስራ እየተከናወነ ይገኛል።
ቀደም ሲል ቴምር ምርትን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት በዓመት 9 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር ይወጣ እንደነበር ያስታወሱት ፕሮፌሰር አሊ አሁን ላይ ቴምርን በሀገር ውስጥ ማምረት በመቻሉ ወደ 650 ሺህ ዶላር ዝቅ ማለቱን አስረድተዋል።
በአለም አቀፍ ደረጃ የቴምር ምርት እና ንግድ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚታይበት ዘርፍ ሲሆን እንደ ግብፅ፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ኢራን፣ አልጄሪያ እና ኢራቅ ያሉ ሀገራት ከፍተኛውን የቴምር ምርት ለዓለም ገበያ የሚያቀርቡ ዋና ዋና አምራቾች ናቸው፡፡SECO


