በኢትዮጵያ የሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) እና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ መካከል የተፈጠረው ውዝግብ ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን፣ ጉዳዩ የሰራተኞችን ሕገ-መንግሥታዊ መብቶች የሚጥስ በመሆኑ የፍትህ ሚኒስቴር በአፋጣኝ ጣልቃ እንዲገባ በይፋ ጥያቄ ቀርቧል።
ውዝግቡ እንዲፈጠር ምክንያት የሆነው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በሥሩ ለሚተዳደሩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ያስተላለፈው የጽሑፍ መመሪያ እንደሆነ ቅዳሜ ገበያ ከምንጮቿ ያገኘችዉ መረጃ ያመለክታል።
በሆልዲንግ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ብሩክ ታዬ ተፈርሞ የወጣው ይኸው ደብዳቤ፤ ተቋሙ የሚያስተዳድራቸውን የልማት ድርጅቶች ውጤታማነት ለማሳደግና ተቋማዊ ሪፎርሞችን ለማከናወን ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ያትታል። ሆኖም የሪፎርም ሥራው ተጠናቆ ተጨማሪ መመሪያ ከሆልዲንጉ እስከሚሰጥ ድረስ፣ አዲስ የሕብረት ስምምነት ከመፈራረም፣ ከማደስ፣ ከመከለስ ወይም በሌላ መልኩ የጋራ ስምምነትን ከማጠናቀቅ ጋር የተያያዙ በሂደት ላይ ያሉ ሥራዎች በሙሉ ለጊዜው ባሉበት እንዲቆሙ ትዕዛዝ አስተላልፏል።
ይህንን ተከትሎ ኢሰማኮ ለፍትህ ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሃና አርአያስላሴ በጻፈው ደብዳቤ፣ የሆልዲንጉ መመሪያ ሠራተኞች በነፃ የመደራጀትና የመደራደር መብት እንዲሁም ኢትዮጵያ ተቀብላ ያፀደቀችባቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሚጥስ ነው በማለት በጽኑ ኮንኗል።
ኮንፌዴሬሽኑ አክሎም፣ በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 42 መሠረት የመንግሥት ሠራተኞች የሥራና የኢኮኖሚ ሁኔታዎችን ለማሻሻል በማህበር የመደራጀት መብት እንዳላቸው በግልጽ ተቀምጧል። ይህ መብት የሠራተኞች ማኅበራትንና ሌሎች ማኅበራትን የማደራጀት፣ እንዲሁም ከአሠሪዎችና ጥቅማቸውን ከሚነኩ ሌሎች ድርጅቶች ጋር በነፃነት የመደራደር መብትን እንደሚያካትት አስታውሷል።
በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 በተደነገገው መሠረት በሁለት ተደራዳሪ ወገኖች ማለትም በድርጅቱና በሠራተኛ ማህበር መካከል የተደረገውን የሕብረት ስምምነት አፈጻጸም የማስቆም፣ ድርድር እንዳይደረግ የማገድ ወይም የማዘገየት በአንድ ወገን ውሳኔ ወይም መመሪያ ሊፈጸም እንደማይችል ኢሰማኮ በይፋ ከፃፈዉ ደብዳቤ ላይ ቅዳሜ ገበያ ተመልክታለች።
ማንኛውም አስፈፃሚ አካል፣ ባለሥልጣንና ድርጅት ሕገ-መንግሥቱን የማክበርና የማስከበር ግዴታ እንዳለበት የጠቆመው ኮንፌዴሬሽኑ፣ ሕግ፣ ደንብና መመሪያ ሲወጣ ሕገ-መንግሥቱን ተቃርኖ ማውጣት ፈጽሞ እንደማይቻል አስገንዝቧል።
በአሁኑ ወቅት ሠራተኛው አባላት ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ባባባሰው የኢኮኖሚ ጫና ውስጥ ወድቆ በሚገኝበት ወቅት፣ በድርድር ሊያገኘው የሚገባውን መሠረታዊ የኢኮኖሚና የሥራ ሁኔታ ማሻሻያ መብት ማሳጣት ተገቢ እንዳልሆነ ማህበሩ ገልጿል።
ይህን ተከትሎ አገሪቱ ጸድቃቸው ከምትገኘው ዓለም አቀፍ የሠራተኛ ድርጅት (ILO) ስምምነቶችና ከሀገሪቱ ሕገ-መንግሥት ጋር ፍጹም የሚጋጨው ይህ የእገዳ መመሪያ፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በተሰጠው ሕጋዊ ሥልጣን መሠረት እንዲሻርና ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ አስፈላጊው የማስተካከያ መመሪያ እንዲሰጥበት ሲል ኢሰማኮ የፍትህ ሚኒስትርን ጠይቋል።SECO


