አንበሳ ባንከ በተፈጠረበት ጫና ብሄራዊ ባንክ ጣልቃ እንዲገባ ጠየቀ


አዲሱ ቦርድ እስካሁን ስራ መጀመር አልቻለም ተብሏል



ባለፈው አመት የተደረገውን ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔዎች በሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎት አጸድቆ አዲሱን ቦርድ ወደ ስራ ለማስገባት አልቻልኩም ሲል የአንበሳ ባንክ ለተቆጣጣሪው አካል አቤት ማለቱ ተሰማ፡፡


ባለፉት ጥቂት አመታት በተለይም ደግሞ ባለፈው አመት ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ገብቶ የነበረው የአንበሳ ባንክ የቦርድ እና ማናጅመንት አመራር በብሄራዊ ባንክ ጣልቃ ገብነት ችግሮቹ የረገቡ ቢመስልም ውጥረቱ አሁንም እንዳልበረደ ETBusinessView ያገኘው መረጃ አመለክቷል፡፡


የመረጃ ምንጮች ለድረ-ገፃችን እንደገለጹት በተለይ ባንኩ ባለፈው አመት እና ቀደም ሲል በነበሩት ወራት በአንዳንድ የቦርድ አባላት እና ተጽእኖ ፈጣሪ ባለአክሲዮኖች በቦርድ እና በማናጅመንት ላይ ከብድር እና የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ጫና ይደረግ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡


በተለይ ቀደም ሲል ከፍ ያለ ብድር ላለባቸው እና የመክፈል ስጋት ላለባቸው ደንበኞች የውጭ ምንዛሬ ጭምር ያለ በቂ ማስያዣ አቅርቡ መባሉ በአመራሩ መካከል ከፍተኛ መከፋፈል እና ግፊት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኖ እንደነበር ያስታወሱት ምንጮች ጉዳዩ ወደ ተቆጣጣሪው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ዘንድ ጭምር መድረሱን ያስታውሳሉ፡፡


ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች ገፊ ምክንያት ቢሆኑም ቦርዱን በመቆጣጠር የፈለጉትን የስራ አመራር በማስቀመጥ ባንኩን ለፈለጉት አላማ ለመዘወር የተደራጁ ሰዎች ለብሄራዊ ባንክ የዛሬ አመት የተደረገውን የጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔዎች ተገቢነት የሌላቸው እና ህጋዊ ስርአቱን ያልተከተሉ ናቸው ሲሉ ከሰው እንደነበር ነው የጠቀሱት፡፡


ባለፈው ጥቅምት 2018 ዓ/ም በተደረገው አመታዊ የባለ አክሲዮኖች ጉባኤ የባንኩን ካፒታል ማሳደግ እና የቦርድ ምርጫን ጨምሮ ሌሎች አጀንዳዎች ቀርበው ውሳኔ የተደረገበት ነበር፡፡


ሆኖም በአንዳንድ የቦርድ አባላት በቀረበ አቤቱታ የጉባኤው ሂደት በተቆጣጣሪው አካል ከተመረመረ እና ከብሄራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ጨምሮ ከማእከላዊ ባንኩ ሃላፊዎች ጋር ውይይት ተደርጎ የቦርድ ምርጫው እንዲደገም፣ ቀሪው የስብሰባው አጀንዳ ቃለ ጉባኤ በቦርድ ተፈርሞ እንዲጸድቅ ውሳኔ ተላልፏል፡፡


ይህን ተከትሎ ብሄራዊ ባንክ ራሱ መርቶ ባካሄደው የቦርድ ምርጫ፣ ምርጫው ከመደረጉ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ማለትም ነሀሴ 1 ቀን 2018 ዓ/ም ማእከላዊ ባንኩ ለአንበሳ ባንክ በላከው ደብዳቤ ለውዝግብ ምክንያት የሆነው የቀደመው ቦርድ እና ጥቅምት ተመርጠው የነበሩ አባላት በሙሉ ነሀሴ 2 ቀን በተደረገው ምርጫ መሳተፍ እንዳይችሉ በማገዱ ሙሉ በሙሉ በእለቱ እጩ ተደርገው የቀረቡ እና ቀደም ሲል ቅስቀሳ ያላደረጉ እና ያልተደረገላቸው አዳዲስ አባላት በቦርድ አባልነት እንዲመረጡ ማድረግ ተችሎ ነበር፡፡


ሆኖም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት ለETBusinessView እንደተናገሩት የዛሬ አመት በተደረገው ጠቅላላ ጉባኤ የተላለፉ እንደ ካፒታል ማሳደግ፣ የአክሲዮን ሽያጭ እና ማዛወር እንዲሁም ባለቤትነትን ወደ ኤሌክትሮኒክስ የመቀየር እና ሌሎች መሰል ውሳኔዎች ወደ ስራ እስካሁን ለማስገባት አልተቻለም ብለዋል፡፡


አክለውም በጠቅላላ ጉባኤ ተቀባይነት ያገኙት ውሳኔዎች ወደ ስራ እንዲገቡ ቦርድ የሚፈርምበት ቃለ ጉባኤ ለሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎት ቀርቦ መፅደቅ ቢኖርበትም በተሰናባቹ ቦርድ ውስጥ ከነበሩ አባላት ሁለቱ እስካሁን ባለመፈረማቸው ቃለ ጉባኤው መጽደቅ እንዳልቻለ ነው የተገለጸው፡፡


እንደ ውስጥ አዋቂ ምንጮች ገለፃ አንበሳ ባንክ ለብሄራዊ ባንክ ባስገባው አቤቱታ በቃለ ጉባኤው ያልፈረሙት አባላት አክሊሉ ገ/ስላሴ (ዶ/ር) እና አሰፋች ሃይለስላሴ ናቸው፡፡


አክሊሉ (ዶ/ር) ቀደም ሲል ብድር ይቅረብ የሚል አቋም ሲያራምዱ ከነበሩ አንዱ እንደነበሩ የገለጹት ምንጮች በአመራሩ እንዲሁም ቦርድ መካከል ተፈጥሮ ከነበረው ቅራኔ ጋር በተያያዘ ስማቸው ጎልቶ የሚጠራ መሆናቸውን አስታውሰዋል፡፡

ሁኔታውን የጠቅላላው ጉባኤ ውሳኔዎች እንዲሁም ባለፈው ነሀሴ የተመረጠው አዲስ ቦርድ ወደ ስራ እንዳይገባ እንቅፋት ለመፍጠር እስከመጨረሻው የሚችሉትን ለመሞከር ሆን ተብሎ የተደረገ ደባ ነው ያሉት ምንጮች፤ በህጉ መሰረት ቃለ ጉባኤው ከግማሽ በላይ ከተፈረመ መጽደቅ እንደሚችል ነው ያስታወሱት፡፡ ሆኖም የተቆጣጣሪው አካል ማለትም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ይሁንታን ማግኘት ይፈልጋል ሲሉ አክለዋል፡፡


በዚህም ምክንያት ነው አንበሳ ባንክ ሁኔታውን ለማሳወቅ ለብሄራዊ ባንክ ደብዳቤ የፃፈው ሲሉ አክለው ገልጸዋል፡፡

ETBUsinessView ከባንኩ አመራርም ሆነ ከ አክሊሉ (ዶ/ር) ስለጉዳዩ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገቸው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።SECO

Related

አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ እና ከፍተኛ የመንግስት የስራ  ሀላፊዎች ከኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ሀላፊነታቸው ተነሱ

ድርጅቱን በቦርድ ሊቀመንበርነት ሲመሩት የነበሩት አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ፣ምክትል  ሰብሳቢ...

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የተሰጠው የእገዳ መመሪያ ውዝግብ አስነሳ​​

በኢትዮጵያ የሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) እና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ...

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች የሦስት እርከን የደመወዝ ጭማሪ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ጸደቀ

የሀገሪቱ ግዙፉ መንግሥታዊ የፋይናንስ ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ...

አዳማ  የፈጣን ስማርት የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ መሙያ  ተጠቃሚ  ሆነች

በአለምሰገድ እስጢፋኖስ ኢትዮ ቴሌኮም በዛሬው ዕለት ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዲስ አበባ...

የኢትዮጵያ የሚዲያ ልህቀት ማዕከል ተመረቀ

“ከማገዳችን በፊት ከአምስቴ በላይ ማስጠንቀቂያ ሰጥተናል!” የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ያስመረቀው...

Popular Categories