በኢትዮጵያ በፋይናንስ፣ በክፍያ ቴክኖሎጂ እና በአቪዬሽን ዘርፎች ግንባር ቀደም የሆኑት ዳሸን ባንክ፣ ማስተርካርድ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሎያሊቲ ፕሮግራም የሆነው ሼባ ማይልስ በጋራ በመሆን አዲስ የፕላቲነም ብራንድ የማስተርካርድ ክፍያ ካርድ ይፋ ማድረጋቸው ተገለፀ።
ጥቅምት 12 ቀን 2019 ዓ.ም. ይፋ የሆነዉ ይህ አዲስ የጋራ ብራንድ ካርድ ደህንነቱ የተጠበቀ ዲጂታል ክፍያን ከሼባ ማይልስ የጉዞ ጥቅማጥቅሞች ጋር በማቀናጀት ለኢትዮጵያውያን ተጓዦች እና ደንበኞች የላቀ የክፍያና የጉዞ ተሞክሮ ለማቅረብ ያለመ መሆኑ ተጠቁሟል።
አዲሱ የፕላቲነም ካርድ በፊዚካል እና በቨርቹዋል አማራጮች የቀረበ ሲሆን፣ የማስተርካርድን ዓለም አቀፍ የክፍያ አቅም፣ የዳሸን ባንክን ዘመናዊ የሱፐር አፕ ቴክኖሎጂ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድን ሰፊ የጉዞ አውታረ መረብ በአንድ ላይ ያስተሳስራል።
ካርዱ ደንበኞች በየዕለቱ ከሚፈጽሟቸው ክፍያዎችና ከጉዞ ጋር በተያያዙ ወጪዎቻቸው ተጨማሪ ማይልስ እና ልዩ ልዩ ጥቅማጥቅሞችን እንዲሰበስቡ እንደሚያስችላቸው ኢቲ ቢዝነስ ቪዉ ሰምታለች።
በይፋዊ የምረቃ ስነ-ስርዓቱ ወቅት እንደተገለጸው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በታመነ የጉዞ ብራንዱ፣ በሰፊው የአፍሪካና ዓለም አቀፍ የበረራ መስመሮቹ እንዲሁም በሼባ ማይልስ ፕሮግራሙ ይሳተፋል። በሌላ በኩል ዳሸን ባንክ የካርድ አሰጣጥ አቅሙን፣ ሰፊ የደንበኞች መሠረቱን እና የዲጂታል መድረኩን ያቀረበ ሲሆን፣ ማስተርካርድ ደግሞ ዓለም አቀፍ የክፍያ አውታረ መረቡን፣ የካርድ ቴክኖሎጂውን እና ለፕሪሚየም ተጠቃሚዎች የተዘጋጁ ልዩ ጥቅማጥቅሞችን አዘጋጅቷል።
የዳሸን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው አለሙ እንደተናገሩት “ዛሬ ደንበኞች የፋይናንስ አገልግሎቶች ከአኗኗራቸውና ከጉዞ ፍላጎታቸው ጋር የተሰናሰኑ፣ ምቹ እና ትርጉም ያለው እንዲሆኑ ይጠብቃሉ። ከማስተርካርድ እና ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ያደረግነው ትብብር የክፍያ፣ የጉዞ እና የሎያሊቲ ጥቅማጥቅሞችን በልዩ መንገድ ያቀናጃል።”
አክለውም ካርዱ በዳሸን ባንክ ሱፐር አፕ በኩል በዲጂታል መንገድ ወይም በፊዚካል ካርድ አማራጭ ማግኘት መቻሉ የደንበኞችን ተሞክሮ የሚያሻሽሉ አዳዲስና ፕሪሚየም የፋይናንስ መፍትሔዎችን ለማቅረብ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
የማስተርካርድ የምሥራቅ አፍሪካ እና የሕንድ ውቅያኖስ ደሴቶች ሲኒየር ቫይስ ፕሬዚዳንት እና ካንትሪ ማናጀር ሚስትር ሼህርያር አሊ በበኩላቸው “በአሁኑ ወቅት ጉዞ ከዲጂታል አገልግሎቶች ጋር እየተቀናጀ ሲሆን፣ ደንበኞችም ከሚፈጽሙት ክፍያ ተመሳሳይ የሆነ ምቾት፣ ደህንነት እና እሴት ይጠብቃሉ። ይህ ልዩ ትብብር የክፍያ አገልግሎትን፣ የሎያሊቲ ፕሮግራምን እና ፕሪሚየም የጉዞ ጥቅማጥቅሞችን በአንድ ላይ በማቀናጀት ለተጓዦች ልዩ የአገልግሎት ተሞክሮ ይፈጥራል” ብለዋል።
ይህ አዲስ የፕላቲነም ካርድ ለተጠቃሚዎቹ በርካታ ልዩ ጥቅማጥቅሞችን ይዞ መጥቷል። ብቁ የሆኑ የካርዱ ተጠቃሚዎች ከማስተርካርድ ኤርፖርት ኤክስፒሪየንስ ጋር በተያያዘ በዓለም ዙሪያ ከ1,600 በላይ የአየር ማረፊያ ላውንጆችን የመጠቀም ዕድል ያገኛሉ። በተጨማሪም በአየር ማረፊያ ፈጣን የማለፊያ አገልግሎት እና ዓለም አቀፍ የዳታ ሮሚንግ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።
ካርዱ በተለይም ለተደጋጋሚ ተጓዦች፣ ለፕሪሚየም ደንበኞች፣ ለንግድ ጉዞ ተጓዦች፣ በውጭ አገራት ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ዲጂታል አገልግሎቶችን በብዛት ለሚጠቀሙ ደንበኞች ቀጣይነት ያለው እሴት ለመፍጠር የተነደፈ ነው። ደንበኞች በበረራ ወቅት ከሚያገኙት ማይልስ በተጨማሪ በዕለት ተዕለት የገበያና የአገልግሎት ክፍያዎቻቸው ላይ ካርዱን በመጠቀም ተጨማሪ የሼባ ማይልስ ነጥቦችን መሰብሰብ ይችላሉ ነዉ የተባለው።
ቨርቹዋል ካርዱ በቀጥታ ከ2 ሚሊዮን በላይ ንቁ ተጠቃሚዎች ባሉት የዳሸን ባንክ ሱፐር አፕ በኩል የሚገኝ ሲሆን፣ ደንበኞች ወዲያውኑ በዲጂታል ክፍያዎች እንዲጠቀሙበት እንደሚያግዛቸው ሰምተናል።
ይህ አገልግሎት በማስተርካርድ እና በዳሸን ባንክ መካከል ባለው ስትራቴጂካዊ ትብብር ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ ፕሮግራሙን በተሳካ ሁኔታ ለማስጀመር የሚደግፍ ስትራቴጂካዊ የኢንቨስትመንት ስምምነትንም የተባለ ሲሆን ይህም ማስተርካርድ በኢትዮጵያ የፕሪሚየም የጉዞ ክፍያ አገልግሎቶች ዘርፍ ያለውን ሥነ-ምህዳር ለማጠናከር እና ዘላቂ እሴት ለመፍጠር ያለውን የረጅም ጊዜ ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ተጠቁሟል።SECO


