ʻበጎ፣ ገንቢ እና ፍሬያማʼ
የተለመደ የፖለቲካ አገላለፅ ነው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ የተጠቀሙት፣ የሶስቱ ሃያላን መሪዎችን ስብሰባ ሲገልፁት፡፡
የዶናልድ ትረምፕ፣ የሺ ጂንፒንግ እና የቭላድሚር ፑቲን የሶስትዮሽ ውይይት ግን ብዙ ጉዳዮችን፣ በርካታ የፖለቲካ አመላካቾችን፣ የሀይል አሰላለፍን እንዲሁም ተጨባጭ ውጤቶችን የያዘ መሆኑ ታላቅ መነጋገሪያ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ስለ ሶስትዮሹ በዝርዝር እነሆ፡-
ሃሳብ አመንጪው ፑቲን
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በፖለቲካ ጥርሳቸውን የነቀሉ የዓለምን ፖለቲካ ከቻይናውም ከአሜሪካው አቻቸውም በላይ ለሩብ ክፍለ ዘመን የኖሩበት ነው፡፡ እናም የስብሰባው ሃሳብ የቀረበው ከሳቸው ነው፡፡ የእስያ ፓሲፊክ የኢኮኖሚ ትብብር 21 ሃገራትን ያቀፈ የፓሲፊክ/ ሰላማዊ ውቅያኖስ ተዋሳኝ ሃገራትን ለማስተባበር የተመሰረተ ሲሆን የ2026 ስብሰባው በቻይና ሸንዘን ከተማ ነው የተካሄደው፡፡ በዚሁ አጋጣሚ እንዲህ ብናደርግ ብለው ሃሳብ ያመጡት ደግሞ ቭላድሚር ፑቲን ናቸው፡፡ የፑቲን ብልህነት እዚህ ጋር ይመጣል፡፡ አሜሪካና ሩስያ ይገናኙ ቢባል የዩክሬንና አውሮፓ ጉዳይ ዋና ትኩረት ይሆናል፣ ቻይና ስትታከልበት ግን ስብሰባው የሃያላን፣ ርዕሰ ጉዳዩም አለም አቀፍ ሆኖ ይከሰታል፡፡ እናም ፑቲን አሜሪካ፣ ቻይና እና ሀገሬ ሩሲያ በጋራ እንምከር ሲሉ ቻይና በእርጋታ ጠበቀች፣ ዶናልድ ትረምፕ ሃሳቡን ሲቀበሉት ፕሬዝዳንት ሺ ስብሰባውን ለማዘጋጀት ተጣደፉ፣ ሶስቱ መሪዎችም ታላቁን ሶስትዮሽ ለማካሄድ በቁ፡፡
የትረምፕ ነገር
ቢሊየነሩ ዶናልድ ትረምፕ በሀገራቸው የአጋማሽ ጊዜ ምርጫ ፓርቲያቸው በርካታ የምክር ቤት ወንበሮችን ማጣቱ ቢያበሳጫቸውም፣ ለሩሲያው ፕሬዝዳንት ስስ ልብ ዓላቸው ተብለው ቢወቀሱም ዳግም ፑቲንን ለማግኘት አላመነቱም፡፡ ትረምፕ 21 ሀገራት ካሉበት አፔክ ይልቅ የሶስቱ ሀገራት ምክክር ታላቅነታችንን ያሳያል፣ ቻይና እና ሩሲያ ላይ ጫና በማሳደር የአሜሪካን ታላቅነት ያጎላል በሚል ስብሰባውን ፈልገውታል፡፡ የቡድን ሰባት ሀገራት ስብስብን፣ የኔቶ ሀገራት ህብረትን፣ የተባበሩት መንግስታትን በተደጋጋሚ የሚተቹት ትረምፕ የሶስትዮሽ መድረኩን የʻእውነተኛ ሃያላንʼ ስብስብ አድርገው እንደሚመለከቱት ይታመናል፡፡

ስብሰባው
መሪዎቹ ከሶስትዮሽ ውይይታቸው አስቀድሞ የተናጥል የሁለትዮሽ ውይይቶችን አከናውነዋል፡፡ አሜሪካና ቻይና፣ አሜሪካና ሩስያ፣ ቻይናና ሩሲያ በነበራቸው ምክክር ሁለትዮሽ ጉዳዮችን ተነጋግረዋል፡፡ ትረምፕ፣ ሺ እና ፑቲን በሶስትዮሽ ስብሰባቸው በዲፕሎማሲ ፕሮቶኮል እኩልነትን በሚወክለው ክብ ጠረጴዛ ዙርያ የተሰባሰቡ ሲሆን ለ90 ደቂቃ የቆየ ውይይት አድርገዋል፡፡ ስብሰባው እንደተጠናቀቀም እጅግ ተምሳሌታዊ የሆነ የሶስትዮች እርምጃ ምናልባትም ʻመንጎማለልʼ አሳይተዋል፣ በተናጥል ከስብሰባው ከመበተን የጋራ ጉዞው በዲፕሎማሲ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው እና የስብሰባውን ወይንም በቀጣይ የሚኖረውን የሶስትዮሽ ሁኔታ በበጎ እንዲገመት የሚያደርገው ነው፡፡
መሪዎቹ በዋናነት በአራት ነጥቦች ላይ ያጠነጠነ ምክክር እንዳደረጉ አሳውቀዋል፡፡ የመጀመሪያው የኒዩክሌር ጉዳይ ሲሆን የኒዩክሌር ጦርነት ማንም አሸናፊ የማይሆንበት በመሆኑ ሊደረግ የማይገባው ነው በሚል ሶስቱ ሃገራት ኒዩክሌርን ሊያሳትፍ የሚችል ግጭት እንዳይከሰት በጋራ እንደሚሰሩ አሳውቀዋል፡፡ በእርግጥ ሶስቱ በርካታ ኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ያላቸው ሀገራት በጦርነት አልያም በውጥረት ውስጥ መኖራቸው ጉዳዩን አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ ሩስያ ለአራት ዓመታት የተራዘመ የዩክሬን ጦርነት ላይ ከመሆኗ ባለፈ ከአውሮፓውያኑ ጋር ያለችበት ውጥረት ኒዩክሌር እስከመጠቀም ያደርሳታል ወይ የሚለው ያሳስባል፡፡ አሜሪካ ከኢራን ጋር ያልተቋጨ ግጭት ውስጥ መኖሯ እና አዲስ ጥቃት ልትከፍት ትችላለች የሚለው ስጋት ኒዩክሌርን አማራጭ ያደርጋል ወይ የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ቻይና ጦርነት ውስጥ ባትሆንም ታይዋንን ለመጠቅለል እየገፋች መሆኑ ለተፅእኖ ማሳረፊያ ኒዩክሌርን ትጠቀም ይሆን የሚሉም አሉ፡፡ እናም የሶስቱ ሀገራት የኒዩክሌር ንግግር በጣም አስፈላጊ እና ውሳኔያቸውም በመልካም የሚታይ ነው፡፡
ሁለተኛው የሶስቱ መሪዎች ርዕስ ነዳጅና ሃይል ሲሆን በተለይም የተጣራ ነዳጅ ዘይት ላይ መክረዋል፡፡ አሜሪካ እና ሩስያ ከፍተኛ ነዳጅ አምራች ሲሆኑ ቻይና ከፍተኛ ነዳጅ ገዢ እና የተጣራ ነዳጅ አምራች በመሆኗ የአለም ኢኮኖሚ ቁልፍ የሆነው ነዳጅ ፍሰት እና ግብይት እንዳይቋረጥ በጋራ እንሰራለን ማለታቸው ከፍተኛ ትርጉም ያለው ነው፡፡ የመካከለኛው ምስራቅ ውጥረት ለሩሲያና አሜሪካ ትልቅ የነዳጅ ገበያ ሲሆን ለቻይና ስጋትነቱ እንዳያይል እና ለአለም ኢኮኖሚ በጋራ መስራት የሀያላኑ አማራጭ ሆኖ መቅረቡ ትልቅ ነጥብ ያደርገዋል፡፡
ሶስተኛ የመሪዎቹ ትኩረት የሆነው የተባበሩት መንግስታት ማሻሻያ ጉዳይ መሪዎቹ ምን እንደሚያደርጉ በግልፅ ያልተናገሩበት ነገር ግን ተቋሙ እንዲሻሻል እንሰራለን ያሉበት ነው፡፡ አሜሪካ፣ ቻይና እና ሩስያ የተባበሩት መንግስታት ዋና ወሳኝ አካል የሆነው የፀጥታው ምክር ቤት አባል ስለሆኑ ያሻቸውን ውሳኔ የሚያሳልፉ ሀገራት ቢሆኑም ምክር ቤቱ ላይ በርካታ ሀገራት ጥያቄ ማንሳታቸው አና ሪፎርም መጠየቃቸው የተባበሩት መንግስታት ማሻሻያን የግድ የሚል በመሆኑ ሃያላኑ ሀገራት እኛም እንደግፈዋለን እንሰራለን የሚል ድፍን ያለ የስምምነት ነጥብ አንስተዋል፡፡
አሜሪካ፣ ቻይና እና ሩሲያ በጋራ የሚስማሙበት የአለም አቀፉ ወንጀለኞች ችሎት ICC ጉዳይን በአራተኝነት የመከሩበት ሲሆን የተቋሙን ተአማኒነት ውድቅ ያደረጉበትን አቋም አንፀባርቀዋል፡፡ ችሎቱ እና ተመሳሳይ ተቋማት ያለ ገደብ ስልጣናቸውን ለመጠቀም የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ተቀባይነት እንደሌለውም መሪዎቹ ተስማምተዋል፡፡ ICC በአሜሪካ ወታደሮች በአፍጋኒስታን ወንጀል ፈፅመዋል ማለቱ እና የእስራኤሉን መሪ ለፍርድ መጠየቁ፣ በሩሲያ ቭላድሚር ፑቲንን መክሰሱ፣ የቻይና አጋር የሆነችው ፊሊፒንስ ፕሬዝዳንትን ችሎቱ ይቅረብልኝ ማለቱ ከሶስቱ ሀገራት ጋር ያቃቃረው እና ተመሳሳይ አቋም እንዲይዙበት ያደረገው ጉዳይ ነው፡፡
በእርግጥ ሶስቱ ሀገራት የተስማሙ ይምሰል እንጅ በታይዋን ጉዳይ፣ በኢራን ግጭት፣ በንግድ ፍትጊያ እና በቴክኖሎጂ እሽቅድድም በርካታ የሚገድቧቸው እና በርካታ ንግግር የሚጠይቋቸው ጉዳዮች አሉ፡፡
ቡድን ሶስት G 3?
የአሜሪካ፣ የቻይና እና የሩሲያ ፕሬዝዳንቶች ስብሰባ በርካታ ተቃውሞ እና ድጋፍ እያስተናገደ ነው፡፡ ተንታኞች እንደቆሙበት ወገን ስብሰባው በቻይና፣ አይ በአሜሪካ አይደለም በሩሲያ አሸናፊነት የተደመደመ ነው እያሉ የተቹ ሲሆን አውሮፓውያን ትረምፕ ለፑቲን የሚያሳዩት ስስ ልብ አሁንም አልተዋጠላቸውም፡፡ አንዳንድ ተቺዎች ደግሞ አውሮፓ ሃያልነቷ እያበቃ ቢሆንም ግትርነት ብቻ እያሳየች እስከመች ትቀጥላለች በሚል እውነተኛው የአለም ኢኮኖሚ እና ወታደራዊ ሃያሎች ህብረት ነው በሚል የቡድን ሶስት ስብስብ ጅማሮ ሲሉ ስብሰባውን ጠቅሰውታል፡፡

ማን ምን አገኘ?
ለቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ መሀከል ላይ ያሉ የዲፕሎማሲ ሃያል እና በየትኛውም ግጭት ገለልተኛ አቋም ባለቤት መሆናቸውን ያስረገጡበት፡፡
ለሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከምዕራቡ አለም እንዳልተገለሉ ያሳዩበት እና በኢኮኖሚና በፖለቲካ መስኮች ተመሳሳይ አቋም የሚጋሩ ወዳጆች እንዳሏቸው ያሳዩበት፡፡
ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትረምፕ ወሳኝ የኒዩክሌር ታጣቂ ሀገራትን የጋራ አቋም ያስያዙበት እና በንግግርም በአካላዊ እንቅስቃሴም የአሜሪካን ሃያልነት ያሳዩበት ተብሎላቸዋል፡፡
ሶስቱም መሪዎች ስኬታማ፣ ገንቢ፣ ዓለም አቀፋዊና ሃገራዊ ጥቅምን ያስጠበቅንበት ያሉት ስብሰባ ሲጠናቀቅ ዶናልድ ትረምፕ ለቡድን 20ሃገራት የቀጣዩ ወር ስብሰባ ሁለቱን መሪዎች ጋብዘዋል፡፡ የቻይናው መሪ መምጣት እርግ ሲሆን ቭላድሚር ፑቲን ለበርካታ ጊዜ ከቀሩበት የቡድን 20 ስብሰባ ለመካፈል በትረምፕ እምነት ጥለው ወደ አሜሪካ ሚያሚ እንደሚያቀኑ የተናገሩ ሲሆን እውነት ይታደማሉ ወይ የሚለው የሚጠበቅ ይሆናል፡፡
እውነት ግን ይህ የፕረምፕ፣ የሺ እና የፑቲን ስብሰባ የቡድን ሶስት ጅማሮ ይሆን?SECO

