የዉሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ልማት ፈንድ ከተቋቋመ ጀምሮ ባለው ሂደት ከተለያዩ የፋይናንስ ተቋማትና የልማት አካላት 23.1 ቢሊየን ብር ሀብት ማሰባሰቡን ገለጸ።
ይህ የተሰበሰበው ገንዘብ በጠቅላላው ለ133 ከተሞች የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቶች ተደራሽ በማድረግ ከ8 ሚሊዮን በላይ ለሚሆን ህብረተሰብ ንጹህ ውሃ እንዲያገኙ አስችሏል።
የውሃ ልማት ፈንድ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ዶጊሶ ጎና ተቋሙ ከተቋቋመ ከ23 ዓመት በላይ መሆኑን አስታውሰው፣ መስፈርቱን ለሚያሟሉ ከተሞች በረጅም ጊዜና ዝቅተኛ ወለድ ብድር በማበደር የንጹህ ውሃ ተደራሽነትን በማስፋት ረገድ ውጤታማ ስራ ተሰርቷል ሲሉም ተናግረዋል።
አሁን ላይ ተቋሙ የብድር አሰጣጡን ይበልጥ ግልጽና ቀልጣፋ ለማድረግ፣ በፈረንሳይ የአማካሪ ልማት ድርጅት ለአንድ ዓመት ሲያስጠናው የቆየውን “የከተሞች ቅድመ መለያ መስፈርት እና የአዋጭነት የጥናት ሰነድ” ለውይይት ማቅረቡ ነዉ የተገለፀው።


