ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ25ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በኃይሌ ግራንድ ሆቴል በድምቀት አከበረ፤ በዓሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)ን ጨምሮ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ አትሌቶችና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት ተከናውኗል።
የ25ኛ ዓመት ክብረ በዓሉ ዋና ማድመቂያ የሆነው ደግሞ፣ የአሜሪካ ባንክ (Bank of America) ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር እ.ኤ.አ ከ2026 ጀምሮ ለአምስት ዓመታት የሚቆይ የአጋርነት ስምምነት መፈራረሙ ነው።
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መስራች ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ በዚህ ወቅት ባስተላለፈው መልዕክት፤ ስምምነቱ ከድርጅቱ ጋር ሳይሆን “ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር የተደረገ” መሆኑን ገልጾ፣ የአሜሪካ ባንክ የታላቁ ሩጫን ዓለም አቀፍ ተደራሽነት ለማስፋት ወደ ኢትዮጵያ ስለመጣ ምስጋና አቅርቧል።
ሻለቃ ኃይሌ አክሎም፣ ይህ አጋርነት የተፈራረምንበት ቀን ትልቁ የደስታዬ ቀን ነው፣ እንዲሁም ስምምነቱ የታላቁ ሩጫን አቅም ለማሳደግ ትልቅ የመሰረት ድንጋይ ነው ብሏል።
በሌላ በኩል፣ የአሜሪካ ባንክ ዓለም አቀፍ የገበያ ትብብር ኃላፊ ብራድ ሮዝ በበኩላቸው፤ ከ”ዓለም አሻራ ከሆነው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ” ጋር ለአምስት ዓመታት ለመስራት በመቻላቸው ኩራት እንደተሰማቸው ገልጸው፣ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አንድነትን የሚፈጥርና የኢኮኖሚ መነቃቃትን የሚያሳልጥ መሆኑን ተናግረዋል።


