የአርባ ምንጭ የአዞ እርባታ ማህበር የአዞ ቆዳና ሥጋን ለዓለም አቀፍ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት የሚያስችለውን ታሪካዊ እርምጃ መውሰዱ ተገለጸ።
ማህበሩ በቅርቡ ከጀርመን ካምፓኒ ጋር የውል ስምምነት የፈረመ ሲሆን፣ በተጨማሪም ለአገር ውስጥ ባለሀብት 500 አዞዎችን ለመሸጥ መዋዋሉን የጋሞ ልማት ማህበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዋኖ ዋሎሌ (ዶ/ር) አስታውቀዋል።
ዋኖ ዋሎሌ እንደገለጹት፤ ማዕከሉ ከተቋቋመ ረጅም ዓመት ቢሆነውም የሚጠበቀውን ያህል ውጤት ማምጣት ሳይችል ቀርቶ እንደነበር ገልጸው፣ ማህበሩ ከተረከበ በኋላ ግን ከፍተኛ መሻሻል ታይቷል።
በማዕከሉ ጥገና መደረጉን ተከትሎ በአሁኑ ጊዜ ከ4 ሺህ በላይ አዞዎች የሚገኙ ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥም 1 ሺህ ያህሉ ለቆዳ እና ለተለያዩ ምርቶች ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ መዘጋጀቱ ነዉ የተገለፀው።
ከአዞ ቆዳ የሚሠሩ ቦርሳ፣ ቀበቶ፣ ዋሌትና የመሳሰሉ ቁሳቁሶች በውድ ዋጋ ስለሚሸጡ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ሊያስገኙ እንደሚችሉ ተመላክቷል።


