የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) በሱዳን ደቡብ ኮርዶፋን ግዛት ውስጥ በሚገኝ የሎጂስቲክስ ማዕከሉ ላይ በትናንትናው ዕለት በደረሰ የድሮን ጥቃት 6 ሰላም አስከባሪዎች መሞታቸውን እና 8 መቁሰላቸውን አስታወቀ።
ጥቃቱ የደረሰው በካዱግሊ በሚገኘው የተመድ ማዕከል ላይ ሲሆን፣ የሞቱት እና የተጎዱት በሙሉ በሱዳን እና በደቡብ ሱዳን ድንበር አካባቢ በአብዬ ለተሰማራው የተመድ ተልዕኮ (UNISFA) የሚያገለግሉ ባንግላዴሻውያን አባላት ነበሩ።
የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ድርጊቱን “አሰቃቂ የድሮን ጥቃት” ሲሉ በጽኑ አውግዘውታል። “የተመድ ሰላም አስከባሪዎችን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶች በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት የጦር ወንጀል ሊሆኑ ይችላሉ” ሲሉ ጉቴሬዝ አስጠንቅቀዋል።
የተመድ የሰላም ማስከበር ኃላፊ ዣን ፒየር ላክሮዋም ይህንን አስተጋብተው “የተመድ ሰላም አስከባሪዎች ዒላማ አይደሉም” ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል።
ይህ ጥቃት ከመድረሱ በፊት፣ አማፂያኑ የፈጥኖ ደራሽ ታጣቂዎች (RSF) ሕዳር 25 ቀን በደቡብ ኮርዶፋን ግዛት በካሎጊ ከተማ በመዋዕለ ሕፃናት እና ሆስፒታል ላይ የድሮን ጥቃት ፈጽመው እንደነበር መዘገቡ ይታወሳል። በሱዳን ባለሥልጣናት መረጃ መሠረት፣ በወቅቱ 43 ሕጻናትን ጨምሮ 79 ሲቪሎች ተገድለዋል። Seco


