ኢትዮጵያ እና ህንድ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ዘርፍ ግንኙነት ያላቸው አገራት ናቸው፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያና ሕንድ የንግድ ትስስር ከፈጠሩ ከ2000 ዓመታት በላይ አስቆጥረዋል።
የኢትዮጵያ እና ህንድ ግንኙነታቸው ዘመናትን እንዳስቆጠረ ምስክር ከሚሆኑ ተግባራት መካከል ሕንድ ከእንግሊዝ ነጻነቷን ከተጎናጸፈች በኋላ ለሕንድ ዕውቅና በመስጥ ቀዳሚዋ አገር ኢትዮጵያ ናት፡፡
ኢትዮጵያ እና ህንድ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1948 ሲሆን ሀገራቱም
ኤምባሲ በመክፈት እስከዛሬ የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ከአፍሪካ ሀገራት በሕንድ ኤምባሲዋን የከፈተችዉ የመጀመሪያዋ ሀገርም ኢትዮጵያ ናት፡፡
ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ሁለት ጊዜ እ.አ.አ በ1956 እና በ1958 በህንድ ያደረጓቸው ኦፊሳላዊ ጉብኝት ለሁለቱ አገራት ግንኙነት መጠናከርና መሰረት እንደሆነም ይጠቀሳል፡፡
የህንድ ህዝብና መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ግንኘነት አንዱ ማሳያ በትምህርት ዘርፍ ያላቸው የሁለትዮሽ ግንኙነት እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያን በሕንድ ትምህርታቸውን የመከታተል ዕድል ሲያገኙ የሕንድ ዜጎች ደግሞ በኢትዮጵያ በመምህርነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል አሁንም በአንዳንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በመምህርነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው በኢትዮጵያ እና ህንድ ማህበረሰብ ድጋፍ የተቋቋመው ጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል የህንድ እና የኢትዮጵያ ወዳጅነትን ወካይ ሆኖ ይታያል።
የህንድ ማህበረሰብ ከፍተኛ ገንዘብ እገዛ በመስጠት የሕክምናው ተቋም ሕንፃ የመገንባቱ ስራ በ1951 የመሠረቱን ድንጋይ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አኖሩ በ1959 ሆስፒታሉ በመደበኛነት አገልግሎት መስጠት እንደጀመረ በሆስፒታሉ ዙሪያ የተጻፉ ድራሳናት ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡
ህንድ በአዲስ አበባ ከተማ በፒያሳ ለቀዳማዊ ኃይለስላሴ ሀውልት ያቆመች ቢሆንም አብዮቱን ተከትሎ ደርግ ሀውልቱ ከቆመበት ስፍራ እንዲነሳ አድርጓል፡፡
ህንድ ከኢትዮጵያ ጋር በንግድ፣ ኢንቨስትመን፣ በባህል፣ መስኮች በትብብር እየሰራች ትገኛለች፡፡
ህንድ እና ኢትዮጵያ ከቅርብ አስርት አመታት ወዲህ ወደ ጠንካራ እና ዘርፈ ብዙ የንግድ እና የኢኮኖሚ አጋርነት ያደገ እና ታሪካዊ ጉልህ ግንኙነት አላቸው።
ህንድ ወደ ኢትዮጵያ ከምትልካቸው ምርቶች ውስጥ ፋርማሲዩቲካልስ፣ ማሽነሪዎች፣ የብረት ውጤቶች፣ ተሸከርካሪዎች፣ የኤሌክትሪክ እቃዎች፣ ፕላስቲኮች እና የወረቀት ውጤቶች በቀዳሚነት ሲጠቀሱ ኢትዮጵያ ደግሞ ወደ ሕንድ ከምትልካቸው ምርቶች መካከል ጥሬ ቆዳና ሌጦ፣ ጥራጥሬ፣ቅመማ ቅመም እና ቡና ቀዳሚውን ይይዛሉ።
ህንድ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ከፍተኛ የውጭ ባለሀብቶች አንዷ ነች። ከ650 በላይ የህንድ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ያፈሰሱ ሲሆን የተፈቀደላቸው ኢንቨስትመንቶች በድምሩ በርካታ ቢሊዮን ዶላር ደርሷል።
የተሰማሩብት ዘርፍም ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ የቆዳ ማቀነባበሪያ፣ ስኳር፣ ግብርና ላይ የተመሰረቱ ኢንዱስትሪዎች፣ ፕላስቲኮች እና ሴራሚክስ፣ግብርና እና የአበባ ልማት ይገኙበታል፡፡ በርካታ የህንድ ኩባንያዎች ትልልቅ የንግድ እርሻዎችን የሚመሩ ሲሆን በኢትዮጵያ ከፍተኛ ትርፍ በሚያስገኝ የአበባ ምርት ኤክስፖርት ኢንዱስትሪ ውስጥ ዋና ተዋናዮች ናቸው።
የህንድ ቴክኒካል እና ኢኮኖሚ ትብብር (ITEC) ኢትዮጵያ ከፍተኛ ተጠቃሚ ነች፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን በህንድ በአስተዳደር፣ በአይቲ፣ በስራ ፈጠራ እና በዲፕሎማሲ የሰለጠኑ ናቸው።
የህንድ-ኢትዮጵያ የንግድ ግንኙነት ያልተመጣጠነ ቢሆንም ህንድ አስፈላጊ የሆኑ ሸቀጦችን፣ ካፒታልን እና ቴክኒካል እውቀትን የምታቀርብ ሲሆን ኢትዮጵያ ትልቅ ስትራቴጂካዊ ገበያ፣ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች የኢንቨስትመንት እድሎችን እና የግብርና ኤክስፖርት ላይ የበኩሏን እየተወጣች ትገኛለች።
እ.አ.አ በ2023/24 በወጣ መረጃ የኢትዮጵያ እና ህንድ የሁለትዮሽ የንግድ ልውውጥ ምጣኔ 271 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡
የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረጉ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ማንሞሃን ሲንግ በ2011 ኢትዮጵያን ከጎበኙ በኋላ ሞዲ በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉ ሁለተኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው።
የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር የሚወያዩ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት በፓርላማ ተገኝተው ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡@seco


