ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካን ብሔራዊ ደህንነት ለማስጠበቅ በሚል የጉዞ እገዳ የተጣለባቸውን አገራት ቁጥር ወደ 39 የሚያሳድግ አዲስ አዋጅ ፈርመዋል።
ይህ ውሳኔ ቀደም ሲል በዝርዝሩ ውስጥ ከነበሩት 19 አገራት በተጨማሪ 20 አዳዲስ አገራትን ያካተተ ሲሆን፣ በታሪክ ከፍተኛው የጉዞ እገዳ ሆኖ ተመዝግቧል።
በአዲሱ አዋጅ መሠረት ደቡብ ሱዳን፣ ሶሪያ፣ ማሊ፣ ኒጀር፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ላኦስ እና ሴራሊዮን በሙሉ የጉዞ እገዳ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ አዳዲስ አገራት ናቸው።
በተጨማሪም እንደ ናይጄሪያ፣ ታንዛኒያ፣ ሴኔጋል፣ ዛምቢያ እና ዚምባብዌ ያሉ 15 አገራት ደግሞ በከፊል እገዳው እንዲካተቱ ተደርጓል።
ዋይት ሀውስ እንደገለጸው፣ እነዚህ አገራት የታገዱት ተጓዦችን በመለየት እና መረጃን በማጋራት ረገድ “ከፍተኛ የደህንነት ጉድለት” ስለታየባቸው ነው።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ይህንን እርምጃ የወሰዱት በዋሽንግተን ዲሲ አንድ የብሔራዊ ጥበቃ አባል በአፍጋኒስታን ተወላጅ መገደሉን ተከትሎ የኢሚግሬሽን ቁጥጥሩን ለማጠናከር የሚያደርጉት ጥረት አካል ነው።
አዲሱ አዋጅ ከሀገራቱ በተጨማሪ በፍልስጤም ባለሥልጣን (Palestinian Authority) የጉዞ ሰነድ በሚጠቀሙ ግለሰቦች ላይም ገደብ ጥሏል።
በአሁኑ ወቅት እገዳው የጸናባቸው 39 አገራት ሲሆኑ፣ ከእነዚህም መካከል እንደ ኤርትራ፣ ሶማሊያ እና ሱዳን ያሉ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ቀደም ሲል በነበሩበት የሙሉ እገዳ ዝርዝር ውስጥ ይገኛሉ።
አዋጁ ሕጋዊ የቋሚ ነዋሪነት ፈቃድ (Green Card) ያላቸውን እና ቀደም ሲል ቪዛ የተሰጣቸውን ግለሰቦች በተመለከተ የተወሰኑ ልዩ ሁኔታዎችን እንደሚፈቅድ ተመልክቷል።@Seco


