የኢትዮጵያና የአሜሪካ መንግስታት በጤናው ዘርፍ ያላቸውን የሁለትዮሽ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግርና ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚቆይ የ1.6 ቢሊዮን ዶላር የጤና ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ተፈራረሙ።
ይህ ስምምነት ከፈረንጆቹ 2026 እስከ 2030 የሚዘልቅ ሲሆን፣ ዋና ዓላማውም በሀገሪቱ የኤችአይቪ/ኤድስ፣ የቲቢ እና የወባ በሽታዎችን ለመከላከል የሚደረገውን ድጋፍ ማስቀጠል ነው።
በተጨማሪም የእናቶች እና ህጻናት ጤናን ለመጠበቅ እንዲሁም የወረርሽኝ ምላሽ እና ዝግጁነት አቅምን በማሳደግ የኢትዮጵያን የጤና ስርዓት ይበልጥ ለማጠናከር ታቅዶ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።
ለዚህ ግዙፍ የጤና ፕሮጀክት ውስጥ 1.6 ቢሊዮን ዶላሩ በአሜሪካ መንግስት የሚሸፈን ሲሆን፣ ቀሪው ፋይናንስ ደግሞ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የሚቀርብ ይሆናል። የኢትዮጵያ መንግስት ድርሻውን የሚሸፍነው የሀገር ውስጥ የጤና ስርዓት ፋይናንስን ለማሳደግ በያዘው ዘላቂ የፋይናንስ እቅድ መሰረት እንደሆነ በስምምነቱ ወቅት ተብራርቷል።
የሁለቱ ሀገራት የረዥም ጊዜ የትብብር ማዕቀፍ የተቀናጀና ለማንኛውም ችግር የማይበገር የጤና ስርዓትን ለመገንባት የሚያስችል መሆኑ ተመላክቷል። ስምምነቱ የዜጎችን ጤና ከማረጋገጥ ባለፈ፣ የጤና ባለሙያዎችን ብቃት እና ክህሎት ለማሳደግ፣ የሀገር ውስጥ የጤና ፋይናንስን ለማጠናከር እንዲሁም የሀገር ውስጥ የመድሀኒት አቅርቦት እና ምርትን በማሳደግ ረገድ የማይተካ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል።@seco


