የዛምቢያ ማዕከላዊ ባንክ ከአውሮፓውያኑ ጥቅምት ወር ጀምሮ የማዕድን ኩባንያዎች የግብር ክፍያቸውን በቻይና የገንዘብ አይነት ‘ሬንሚንቢ’ (ዩዋን) መፈጸም መጀመራቸውን አረጋገጠ።
በአፍሪካ ሁለተኛዋ ግዙፍ የመዳብ አምራች የሆነችው ዛምቢያ ይህንን ውሳኔ ያሳለፈችው፣ ቻይና የሀገሪቱ ዋነኛ የመዳብ ገዥ እና ትልቁ አበዳሪ በመሆኗ እንዲሁም ባንኩ የውጭ ምንዛሬ ክምችቱን ለማስፋፋት ባለው ስትራቴጂ መሰረት መሆኑ ተጠቁሟል። ይህ አዲስ አሰራር ዛምቢያ ለቻይና ያለባትን ዕዳ በዩዋን እንድትከፍል በማስቻል የምንዛሬ ወጪን እንደሚቀንስላት ታምኖበታል።
ይህ የዛምቢያ እርምጃ ቻይና ገንዘቧን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስፋፋት የምታደርገውን ጥረት የሚያግዝ ሲሆን፣ መሰል አዝማሚያዎች በሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም እየታዩ ነው። ለምሳሌ ኬንያ ከቻይና የተበደረችውን የ5 ቢሊዮን ዶላር የባቡር መስመር ግንባታ ዕዳ ወደ ዩዋን በመቀየር በዓመት 250 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ለማዳን እየሰራች ሲሆን፣ ኢትዮጵያም በተመሳሳይ ሁኔታ 5.38 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋውን የቻይና ዕዳዋን ወደ ዩዋን ለመቀየር ንግግር መጀመሯ ተገልጿል።@SECO


