የቬትናም ጠቅላይ ሚኒስትር ፋም ሚን ቺን ከሩሲያ ጋር የሚካሄደው የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ግንባታ ድርድር እስከዚህኛው ጥር ወር መጨረሻ ድረስ እንዲጠናቀቅ ጥሪ አቀረቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን መመሪያ ያስተላለፉት ጃፓን በሁለተኛው የኒውክሌር ፕሮጀክት ላይ የነበራትን ተሳትፎ ማቋረጧን ተከትሎ ሲሆን፣ ባለሥልጣናት የጃፓንን ቦታ የሚተካ አዲስ አጋር አገር በአስቸኳይ እንዲፈልጉም አሳስበዋል።
ጃፓን ከፕሮጀክቱ ለመውጣት የወሰነችው ቬትናም እ.ኤ.አ. በ2035 ማመንጫውን ሥራ ለማስጀመር የያዘችው ዕቅድ እጅግ አዳጋችና ሊሳካ የማይችል መሆኑን በመጥቀስ እንደሆነ በሃኖይ የጃፓን አምባሳደር ናኦኪ ኢቶ ገልጸዋል።
ቬትናም በ2016 አቋርጣው የነበረውን የኒውክሌር ኃይል መርሃ ግብር ባለፈው ዓመት ዳግም የጀመረችው፣ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ የመጣውን የኤሌክትሪክ ፍላጎት ለማሟላት በማለም ነው።
እንደ ሳምሰንግ እና አፕል ያሉ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች መሸሸጊያ የሆነችው አገሪቱ፣ በተደጋጋሚ በሚከሰት የኃይል መቆራረጥ ሳቢያ የኢንዱስትሪ ዘርፏ ፈተና ውስጥ ወድቋል።
ምንም እንኳን አገሪቱ ከታዳሽ ኃይልና ከጋዝ የሚገኝ ኤሌክትሪክን ለማሳደግ ጥረት ብታደርግም፣ የሕግ ማዕቀፎችና የዋጋ ተመንን የመሳሰሉ እንቅፋቶች ለፕሮጀክቶቹ መዘግየት ምክንያት ሆነዋል። አሁን ባለው አዲስ መመሪያ መሠረት፣ ሁለቱ የኒውክሌር ጣቢያዎች እ.ኤ.አ. ከ2031 በኋላ ወደ ሥራ እንዲገቡ ግብ ተቀምጧል።@SECO


