የአሜሪካ መንግሥት በብረት ውጤቶች ላይ ሊጥል ያለው አዲስ የታሪፍ (ቀረጥ) ጫና፣ በዓለም አቀፍ የመዳብ ገበያ ላይ ከፍተኛ መዛባት እየፈጠረ ይገኛል። በተለይም በቻይና ወደቦች በሚገኙ መጋዘኖች ውስጥ ተከማችቶ የነበረው መዳብ በከፍተኛ መጠን ወደ አሜሪካ እየተጓጓዘ በመሆኑ፣ በቻይና የብረት አቅርቦት ላይ እጥረት መፈጠሩ ተነግሯል።
በአሜሪካ የንግድ ልውውጥ ማዕከል የሚታየው የመዳብ ዋጋ፣ በለንደን ብረት ልውውጥ ካለው ዋጋ በእጅጉ ብልጫ አሳይቷል። ይህ የዋጋ ልዩነት ነጋዴዎች ብረትን ከቻይና እና ከሌሎች የዓለም ክፍሎች ወደ አሜሪካ በመላክ ከፍተኛ ትርፍ እንዲያገኙ በር ከፍቷል።
በዚህም ምክንያት ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት 2025 የቻይና የተጣራ መዳብ ወደ ውጭ የሚላከው መጠን ታሪካዊ የተባለለትን ከፍተኛ ደረጃ መያዙን የሮይተርስ የገበያ ትንታኔ ያመለክታል።
በህዳር ወር ብቻ ቻይና 143,000 ሜትሪክ ቶን መዳብ ወደ ውጭ የላከች ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉ በቀጥታ ወደ አሜሪካ የተጓጓዘ ነው።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በብረት ላይ ቀረጥ ሊጥል ይችላል የሚለው ስጋት፣ ብረቱ አስቀድሞ ወደ አሜሪካ እንዲገባ አድርጓል። ይህም በሻንጋይ እና በሌሎች የቻይና ወደቦች ባሉ የንግድ ቀጠናዎች ተከማችቶ የነበረውን ብረት እያሟጠጠው ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ መጋዘኖች ያለው የመዳብ ክምችት ከ450,000 ቶን በላይ የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ከለንደን እና ከሻንጋይ የገበያ ማዕከላት ድምር ክምችት የላቀ ሆኖ ተመዝግቧል። ይህ የክምችት ሽግግር በሌሎች የዓለም ክፍሎች በተለይም በአውሮፓ የአቅርቦት እጥረት እና የዋጋ ንረት እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል።@SECO


