የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የብድር ጥያቄ በሚቀርብበት ወቅት የሚቀርቡ የፕሮጀክት አዋጭነት ጥናቶች ጥራትና ደረጃቸውን ያልጠበቁ መሆናቸው ለብድር አሰጣጡ ሂደት እንቅፋት እየሆነ መምጣቱን ገለጸ።
ባንኩ ይህንን ስጋት የገለጸው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከ13 ዋና ዋና የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ተወካዮችና ከንግድ ባንክ የሥራ ኃላፊዎች ጋር የብድር አቅርቦት ተግዳሮቶችን ለመፍታት ባደረጉት የምክክር መድረክ ላይ ነው።
በውይይቱ ወቅት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በኢትዮጵያ ውስጥ ለኢንዱስትሪ ዘርፉ የተለየ የኢንቨስትመንት ባንክ ባለመኖሩ፣ አምራቾች ለካፒታል ብድር በፖሊሲ ባንኮች በተለይም በንግድ ባንክ ላይ ብቻ ጥገኛ መሆናቸው ትልቅ ክፍተት መፍጠሩን ጠቁመዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም የፋብሪካ ግንባታ ለማካሄድ መሬት የተረከቡ አንዳንድ ባለሀብቶች በፋይናንስ እጥረት ምክንያት ወደ ሥራ መግባት ባለመቻላቸው፣ ይህም በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም ባንኩ የአገልግሎት አሰጣጡን በማዘመንና የብድር ሂደቱን በማቀላጠፍ አምራቾችን ሊደግፍ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በሌላ በኩል በውይይቱ የተሳተፉ የአምራች ዘርፉ ተወካዮች ባንኩ የብድር ጥያቄዎችን የሚገመግምበት መንገድ እጅግ ዘገምተኛና ወጥነት የጎደለው መሆኑን፣ እንዲሁም የቀረቡ ጥናቶችን በሚገመግሙ ባለሙያዎች መካከልም የተመጣጠነ ግንዛቤ አለመኖር ለሥራቸው እንቅፋት እንደሆነባቸው ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
ለቀረቡት ቅሬታዎች ምላሽ የሰጡት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ደረጄ ፉፋ፣ ብዙዎቹ በአምራቾች የሚቀርቡ የጥናት ሰነዶች ጥራታቸው የወረደ፣ ከሌሎች ዘርፎች የተቀዱና የባንኩን መመሪያዎች ያላገናዘቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ይህ ችግር የብድር ሂደቱን ከማጓተቱም በላይ የፕሮጀክቶቹን አዋጭነት ለመመዘን አስቸጋሪ እንደሚያደርገው አስረድተዋል። ባንኩ ይህንን ችግር ለመፍታትና የብድር አሰጣጡን ውጤታማ ለማድረግ የቁጥጥር ሥርዓቱን ለማዘመን እያቀደ መሆኑን የገለጹት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፣ ባለሀብቶችም ደረጃውን የጠበቀና ተአማኒነት ያለው የጥናት ሰነድ እንዲያቀርቡ አሳስበዋል።@SECO


