የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዳያስፖራው ማህበረሰብ አባላት በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚያቋቁሟቸው ከትናንሽ እስከ ትላልቅ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች አስፈላጊውን የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ በቂ ዝግጅት ማድረጉን አስታወቀ።
የባንኩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከኢትዮ-አሜሪካ የንግድ ምክር ቤት ተወካዮችና ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከፍተኛ የቢዝነስ ልኡካን ቡድን ጋር በነበራቸው ውይይት እንደገለጹት፤ ባንኩ ለዳያስፖራው ማህበረሰብ የሚሰጣቸውን ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች ይበልጥ ለማሳደግ እየሰራ ይገኛል።
የባንኩ የኮርፖሬት አገልግሎቶች ኤክስኪዩቲቭ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት፤ ባንኩ ቀደም ሲል በትላልቅ የመንግስት የልማት ፕሮጀክቶች ላይ የነበረውን ከፍተኛ የፋይናንስ አቅርቦት አሁን ላይ ወደ ግል ሴክተሩ አዙሯል። በዚህም የዳያስፖራው ማህበረሰብ ወደ ሀገር ቤት ይዞት ለሚመጣው የኢንቨስትመንት ሃሳብ ባንኩ የብድር አቅርቦት በማመቻቸት ፕሮጀክቶቹን ለውጤት ለማብቃት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም ባንኩ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አሁን ለደረሰበት ደረጃ የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ ረገድ የነበረውን ግንባር ቀደም ሚና ያብራሩት ኃላፊው፤ በቀጣይም በአሜሪካና በአውሮፓ ከሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት ጋር ተመሳሳይ ውይይቶችን ለማድረግ ዕቅድ መያዙን ገልጸዋል።
የኢትዮ-አሜሪካ የንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ኤልያስ ወልዱ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የውጭ ኢንቨስትመንትን ወደ ሀገር መሳብ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለዚህም ስኬት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በቅርበት መስራት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።@SECO


