የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ውስጥ ለሀገር ውስጥ ገበያ ካቀረባቸው ምርቶች ከ13.4 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን አስታውቋል።
ይህ አፈጻጸም በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ላይ ከታቀደው 8.5 ቢሊዮን ብር እቅድ በእጅጉ የላቀ ሲሆን፣ ባለሀብቶች በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖችና በፓርኮች ውስጥ ያመረቷቸውን ምርቶች ለገበያ በማቅረባቸው የተገኘ ውጤት ነው።
ለዚህ ገቢ ማደግ በመንግስት በኩል የተደረጉ የማሻሻያ ስራዎች ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ሲሆን፣ የምርት መጠኑም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ61 በመቶ ዕድገት ማሳየቱ ተመላክቷል።
በተጨማሪም ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው ቀጠናዎች ውስጥ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 74 ድርጅቶች ከ4,800 በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች ዘላቂ የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ ተደርጓል።
በዚህም የገበያ ትስስር ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት መፈጸም የተቻለ ሲሆን፣ ይህም የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት በበቂ ሁኔታ እንዲቀርብ አስችሏል።
ኮርፖሬሽኑ የምርት አቅርቦቱ ቀጣይነት እንዲኖረው በትኩረት እንደሚሰራ ገልጾ፣ ይህም ለሀገር ውስጥ ገበያ መረጋጋትና ለውጭ ምርት ምትክነት ትልቅ ሚና እንደሚጫወት አስታውቋል።@SECO


