ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ እና የቻይና የልማት ፈንድ ድጋፎች እየቀነሱ በመምጣታቸው፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና ሳዑዲ አረቢያ በአፍሪካ የንፁህ ኢነርጂ ዘርፍ ዋነኛ የገንዘብ ምንጭ በመሆን ብቅ ብለዋል።
Clean Air Task Force (CATF) የተሰኘው ተቋም ይፋ ባደረገው አዲስ ሪፖርት መሠረት፣ ከ2010 ጀምሮ እነዚህ የባሕረ ሰላጤው አገራት በአፍሪካ ለሚከናወኑ የታዳሽ ኃይል ፕሮጀክቶች ከ175 ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት ለማድረግ ቃል ገብተዋል። ይህም አፍሪካ እስከ 2030 ድረስ የኢነርጂ ፍላጎቷን ለማሟላት ለሚያስፈልጋት የ133 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ በጀት እንደ ትልቅ ግብዓት የሚታይ ነው።
ሪፖርቱ አክሎም፣ የገልፍ አገራት የሚከተሉት የኢንቨስትመንት ሞዴል አገራቱን ለከፍተኛ ዕዳ ከሚዳርግ ብድር ይልቅ በቀጥታ በፕሮጀክቶችና በሽርክና ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ለአህጉሪቱ የኢንዱስትሪ ዕድገት ምቹ መሆኑን ያመላክታል።
ይሁን እንጂ ይህ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በአህጉሪቱ ያለውን የኃይል አቅርቦት ክፍተት ለመሙላት ትልቅ ተስፋ ቢኖረውም፣ የራሱ የሆኑ ስጋቶችም ተደቅነውበታል።
በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ከ600 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት የማያገኙ ቢሆንም፣ አህጉሪቱ ከዓለም አቀፍ የንፁህ ኢነርጂ ኢንቨስትመንት የምታገኘው ድርሻ 2 በመቶ ብቻ ነው።
የገልፍ አገራት ኢንቨስትመንት ይህንን ክፍተት ለመድፈን ያለመ ቢሆንም፣ ተንታኞች እንደሚሉት ኢንቨስትመንቱ በጥቂት አገራት ላይ ብቻ ካተኮረ በአህጉሪቱ ያለውን የኢነርጂ ተጠቃሚነት ልዩነት ሊያባብሰው ይችላል።
በመሆኑም እነዚህን ኢንቨስትመንቶች ፍትሃዊ በሆነ መልኩ በጂኦግራፊያዊ ቀጣናዎች በማሰራጨት፣ የረጅም ጊዜ እና ሥርዓታዊ ለውጥ የሚያመጡ አሠራሮችን መዘርጋት ለአፍሪካ የኢነርጂ ነፃነትና ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ግቦች ስኬት ወሳኝ መሆኑ በሪፖርቱ ተመላክቷል። @SECO


