በዓለም አቀፍ ደረጃ በጤናው ዘርፍ የተመዘገቡ ታሪካዊ ስኬቶች ከፍተኛ አደጋ ላይ መውደቃቸውን ዘ ላንሴት ግሎባል ኸልዝ የተባለው የሕክምና መጽሔት በቅርቡ ይፋ ያደረገው ጥናት ያመለክታል።
እንደ አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ እና እንግሊዝ ያሉ ዋና ዋና ለጋሽ አገራት በዓለም አቀፍ እርዳታ ላይ እያደረጉት ያለው ከፍተኛ የበጀት ቅነሳ፣ እስከ አሰርቱ ማብቂያ ድረስ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት ውስጥ እስከ 22.6 ሚሊዮን የሚደርሱ ተጨማሪ የሞት አደጋዎችን ሊያስከትል እንደሚችል ተተንብዮአል።
ይህ ቀውስ በተለይ በሕፃናት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት እጅግ የከፋ ሲሆን፣ ድጋፉ አሁን ባለው ፍጥነት መቀነሱን ከቀጠለ ብቻ እስከ 2030 ድረስ የ5.4 ሚሊዮን ሕፃናት ሕይወት ሊቀጠፍ እንደሚችል ጥናቱ ያስጠነቅቃል።
ባለፉት ሁለት አሰርታት ውስጥ ይፋዊ የልማት እርዳታ (ODA) የሕፃናትን ሞት በ39 በመቶ ለመቀነስ እና እንደ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ያሉ ተላላፊ በሽታዎችን ለመቆጣጠር ወሳኝ ሚና ተጫውቷል። ሆኖም እ.ኤ.አ. በ2024 እና 2025 የታየው ድንገተኛ የገንዘብ ድጋፍ ማቋረጥ፣ በተለይም እንደ አሜሪካ ባሉ ትልልቅ ለጋሾች የሚታየው እስከ 83 በመቶ የሚደርስ የፕሮግራም ቅነሳ፣ እነዚህን ስኬቶች ወደ ኋላ የመመለስ አቅም አለው።
ይህ “የሕይወት መስመር” መቋረጡ እንደ ተቅማጥ፣ ወባ እና የሥርዓተ-ምግብ እጥረት ያሉ በቀላሉ ሊከላከሏቸው የሚችሉ ችግሮች ዳግም እንዲያንሰራሩ በማድረግ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ንጹሃንን በተለይም ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት የሚገኙ ዜጎችን ለሞት ይዳርጋል።
ለጋሽ አገራት የውስጥ በጀታቸውን ለማመጣጠን የሚወስዱት የኢኮኖሚ እርምጃ በድሃ አገራት ላይ የሰው ልጅ ሕልውና ቀውስ እየፈጠረ ይገኛል ተብሏል።
ጥናቱ እንደሚያሳየው፣ ዓለም ከዚህ እልቂት ሊተርፍ የሚችለው ቢያንስ የ2023ቱን የገንዘብ ድጋፍ መጠን ሳይቀንስ በማስቀጠል ብቻ ነው። ዛሬ በገንዘብ ቁጠባ ስም የሚወሰዱ እርምጃዎች ነገ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ሕፃናት ሕይወት የሚለካ ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍሉ በመሆናቸው፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፉን እንዲያጠናክር ሳይንሳዊ ማስረጃው ግልጽ ጥሪ አቅርቧል።@SECO


