የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት ምርቶቻቸውን ያለ ቀረጥ ወደ አሜሪካ ገበያ እንዲያስገቡ የሚፈቅደውን የ”አጎዋ” ስምምነት እስከ ታኅሣሥ 10 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ እንዲራዘም የሚደነግገውን ሕግ ማክሰኞ ጥር 26 ቀን 2018 ዓ.ም ፈርመዋል።
ይህ ውሳኔ ስምምነቱ ካበቃበት መስከረም 2018 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ኋላ ተፈፃሚነት እንዲኖረው ተደርጎ የተራዘመ ቢሆንም፣ የአሜሪካ መንግሥት ግን በአዲሱ ስምምነት ላይ ጠንከር ያሉ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጧል።
መጀመሪያ ላይ የተወካዮች ምክር ቤት ስምምነቱ ለሦስት ዓመት እንዲራዘም ወስኖ የነበረ ቢሆንም፣ ሴኔቱ ግን የትራምፕን “አሜሪካ ትቅደም” ፖሊሲ በመከተል የጊዜ ገደቡን ወደ አንድ ዓመት ዝቅ አድርጎታል።
እንደ አዲሱ መመሪያ አፍሪካውያን ሀገራት ለምርቶቻቸው ቀረጥ ነፃ ዕድል ማግኘታቸውን እንዲቀጥሉ፣ የአሜሪካ የንግድ ድርጅቶች፣ ገበሬዎችና አርቢዎች ወደ አፍሪካ ገበያ ሰፊና ያልተገደበ ተደራሽነት እንዲኖራቸው ይጠበቃል።
የአሜሪካ የንግድ ተወካይ ጃሚሰን ግሪር እንደገለጹት፣ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የአጎዋ ስምምነት ከአፍሪካ የንግድ አጋሮች የበለጠ ነገር የሚጠይቅና ለአሜሪካ ቢዝነስ ዘርፍም የላቀ የገበያ ዕድል የሚያስገኝ መሆን አለበት።
በዚህም መሠረት አፍሪካውያን የአሜሪካ ምርቶች ወደ ሀገራቸው እንዳይገቡ የጣሏቸውን ማናቸውንም የንግድ እንቅፋቶች እንዲያነሱ ይገደዳሉ።
ምንም እንኳን ይህ አጭር ጊዜ ማራዘሚያ ለአፍሪካ ላኪዎች የተወሰነ እፎይታ ቢሰጥም፣ የስምምነቱ ጊዜ ለአንድ ዓመት ብቻ መሆኑና የተቀመጡት አዳዲስ መስፈርቶች ለረጅም ጊዜ የንግድ ዕቅድ ለማውጣት አዳጋች እንደሚሆንባቸው የዘርፉ ባለሙያዎች እየገለጹ ይገኛሉ።@SECO


