የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ) የአሜሪካው የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ካለበት ወደ 4 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ዕዳ ውስጥ ምን ያህሉን እና መቼ እንደሚከፍል በመጠባበቅ ላይ መሆኑን ገለጸ።
የድርጅቱ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ባለፈው ሳምንት ባስተላለፉት ማስጠንቀቂያ፣ ሁሉም አባል አገራት መደበኛ መዋዟቸውን ካልከፈሉ ድርጅቱ ለከፋ የፋይናንስ ውድቀት እንደሚጋለጥ ገልጸው ነበር።
እንደ ተ.መ.ድ መረጃ አሜሪካ ለመደበኛ የሥራ ማስኬጃ 2.196 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም ለሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች 1.8 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ያለባት ሲሆን፣ ይህም ለድርጅቱ መደበኛ በጀት ካልተከፈለው ዕዳ ውስጥ 95 በመቶውን ይይዛል።
በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ዋልትዝ የትራምፕ አስተዳደር በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ቅድመ-ክፍያ ለመፈጸም ማቀዱን ቢገልጹም፣ ትክክለኛው የገንዘብ መጠን ግን ገና አልተወሰነም።
የድርጅቱ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ ዋና ፀሐፊው ከአምባሳደር ዋልትዝ ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ ግንኙነት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል። ዋና ፀሐፊው በደብዳቤያቸው እንዳሳሰቡት፣ ድርጅቱ ለመደበኛ የሥራ ማስኬጃ የሚጠቀመው ጥሬ ገንዘብ እስከ ሐምሌ ወር ድረስ ሊያልቅ ስለሚችል ይህም በዓለም አቀፍ እንቅስቃሴዎች ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል ይፈጥራል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ድርጅቱ ውጤታማ አይደለም በሚል በተደጋጋሚ ሲተቹ የቆዩ ሲሆን፣ አስተዳደራቸውም በ2025 ምንም ዓይነት ክፍያ አለመፈጸሙ ይታወሳል።@SECO


