የአሜሪካ ኮንግረስ የበጀት ቢሮ ባወጣው ሪፖርቱ እንደገለጸው፣ የፌዴራል መንግሥቱ በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር እና በሪፐብሊካኖች ቁጥጥር ስር ባለው ኮንግረስ ስር የሚከተለው የበጀት ጉድለት እየጨመረ በመምጣቱ የሀገሪቱ ብሔራዊ ዕዳ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ውስጥ 64 ትሪሊዮን ዶላር ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።
ተቋሙ በያዝነው የፋይናንስ ዓመት ብቻ ሀገሪቱ 1.9 ትሪሊዮን ዶላር የበጀት ጉድለት እንደሚያጋጥማት የጠቆመ ሲሆን፣ ይህም ዓመታዊ ጉድለት እ.ኤ.አ በ2036 ወደ 3.1 ትሪሊዮን ዶላር ከፍ እንደሚል አመልክቷል። በአሁኑ ወቅት የአሜሪካ አጠቃላይ ዕዳ ከ38 ትሪሊዮን ዶላር በላይ መሆኑ ይታወቃል።
ለዚህ የበጀት ጉድለት መስፋፋት በምክንያትነት የተጠቀሱት ባለፈው በጋ በሪፐብሊካኖች የጸደቀው የግብር እና የወጪ ፓኬጅ እንዲሁም የትራምፕ ጥብቅ የኢሚግሬሽን ፖሊሲዎች ናቸው።
እነዚህ እርምጃዎች በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ውስጥ የበጀት ጉድለቱን በብዙ ትሪሊዮን ዶላሮች የሚጨምሩ ሲሆን፣ ይህም ፕሬዝዳንቱ ከንግድ ታሪፎች (Tariffs) ያገኛሉ ተብሎ የሚጠበቀውን የ3 ትሪሊዮን ዶላር ገቢ ሙሉ በሙሉ ውጤት አልባ እንደሚያደርገው ተገልጿል።
በተጨማሪም የብድር ወለድ ክፍያ መጨመር እና ለማኅበራዊ ደህንነት ፕሮግራሞች የሚወጣው ወጪ በመንግሥት ገቢ እና ወጪ መካከል ያለውን ልዩነት ይበልጥ እያሰፋው ይገኛል።
ከሀገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም አንፃር ሲታይም፣ የሕዝብ ዕዳ ድርሻ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምር ሪፖርቱ አመልክቷል። በዚህ መሠረት የፌዴራል ዕዳ ከሀገሪቱ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) አንፃር ያለው ድርሻ በያዝነው ዓመት ካለበት 101 በመቶ ተነስተው በአንድ አስር ዓመት ውስጥ ወደ 120 በመቶ ከፍ ይላል።
ይህም እ.ኤ.አ በ1946 ተመዝግቦ ከነበረው የ106 በመቶ ከፍተኛ ሪከርድ በላይ ነው። ምንም እንኳን ትራምፕ የፈረሟቸው የሕግ ረቂቆች በዚህ ዓመት የኢኮኖሚ እድገትን ያነቃቃሉ ተብሎ ቢታመንም፣ የታሪፍ ጫናዎች እና የኢሚግሬሽን ቁጥጥር እርምጃዎች በኢኮኖሚው ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ ይህንን እድገት ሊገታው እንደሚችል ተተንብዮአል።@SECO


