የአውሮፓ እና የቻይና መሪዎች የየራሳቸውን ገንዘቦች (ዩሮ እና ዩዋን) በዓለም አቀፍ የንግድና የፋይናንስ መድረክ ላይ ያላቸውን ሚና ለማሳደግ የሚያደርጉት ጥረት የዶላርን ዋጋ እያዳከመው መሆኑ ተነገረ።
የሮይተርስ ዘገባ እንደሚያመለክተው፣ የአሜሪካ ዶላር በዩሮ እና በቻይናው ዩዋን ላይ ያለው የመለወጫ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ ይገኛል።
የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ ዩሮን ከቀጠናው ውጭ በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ አዳዲስ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦቶችን እያመቻቸ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ቻይናም ዩዋን በዓለም አቀፍ ክምችትና ንግድ ውስጥ “ጠንካራ ገንዘብ” ሆኖ እንዲወጣ በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኑ ለዶላር መንሸራተት ዋነኛ ምክንያቶች ተብለዋል።
ይህ የገንዘቦች ዋጋ ለውጥ በዋሽንግተን በኩልም ተቀባይነት ያገኘ ይመስላል ተብሏል። የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ስኮት ቤሰንት “ጠንካራ ዶላር” የሚለው መርህ ከፖሊሲ ጥንካሬ ጋር የተያያዘ እንጂ የግድ ከመለወጫ ዋጋ መናር ጋር እንደማይገናኝ በተደጋጋሚ መግለጻቸው፣ አሜሪካ ለኤክስፖርት ዕድገት ሲባል የዶላር ዋጋ መቀነሱን እንደማትቃወም ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።
ይሁን እንጂ ባለሀብቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ከዶላር ይልቅ ወደ ዩሮ እና ዩዋን ቦንዶች እያዘነበሉ መሆናቸው፣ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ የነበረው የዶላር የበላይነት አዲስ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ይጠቁማል።@SECO


