በኢቢቪ ዘጋቢ
የኢፌዲሪ የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን በሁሉም የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ የአካዳሚክ፣ የምርምር እና የአስተዳደር ሰራተኞች የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጫና የአቻ ግመታ ማስገዳጅ መሆኑን አሳውቋል።
ባለሥልጣኑ ይህንን መመሪያ ተግባራዊ የሚያደርገው በአዋጅ ቁጥር 1263/2014 መሰረት ሲሆን፣ ዋነኛ ዓላማውም በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የሚደረጉ ጥቅማ ጥቅሞችን ለመቆጣጠር እና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እንደሆነ ተገልጿል።
በመመሪያው መሰረት ማንኛውም የመንግስት ዩኒቨርሲቲ ሰራተኛ ከግል የትምህርት ተቋማት ያገኘው የትምህርት ማስረጃ ካለ ቅድሚያ በመስጠት ማስረጃውን ማረጋገጥ ይኖርበታል።
በተመሳሳይ ከውጭ ሀገር የትምህርት ማስረጃ ያላቸው ሰራተኞችም የግድ “የአቻ ግመታ” (Equivalence) ማሰራት እንዳለባቸው ባለሥልጣኑ አሳስቧል።
የዩኒቨርሲቲ አመራሮችም ሰራተኞቻቸው ስለ ማስረጃ አሰጣጥና ማረጋገጫ በቂ መረጃ እንዲኖራቸው የማገዝ እና ሂደቱ ያለእንግልት እንዲከናወን የማድረግ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የትምህርት ማስረጃው ሳይረጋገጥ የሚሰጥ ቅጥር፣ የደረጃ እድገት፣ የጥቅማ ጥቅም አበል እና ማንኛውም ውድድር በህግ የሚያስጠይቅ መሆኑ በጥብቅ ተገልጿል።@SECO
#ቅዳሜገበያ


