በኢቢቪ ዘጋቢ
ኢትዮጵያ የባህር በር አልባ መሆኗና ከወደብ ጋር የተያያዙ ከፍተኛ ገደቦች መኖራቸው፣ ሀገሪቱ በዓመት ከ19 ቢሊዮን እስከ 31 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ የሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት እንድታጣ እያደረጋት መሆኑን የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት (PSI) ይፋ ባደረገው አዲስ ጥናት አመለከተ።
ኢንስቲትዩቱ ባካሄደውና “ባህር ላይ ሉዓላዊነትን ማስመለስ፦ ኢትዮጵያ ለሉዓላዊ የወደብ ተጠቃሚነት የምታቀርበው ሕጋዊ ጥያቄ ታሪካዊ፣ ጂኦ-ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ አስፈላጊነቶች” በሚል ርዕስ በቀረበው ጥናት፣ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እያደገ በመጣ ቁጥር ከወደብ አልባነት ጋር የተያያዙ የአሰራር መጓተቶችና ወጪዎችም አብረው እየጨመሩ መምጣታቸው ተመልክቷል።
እንደ ጥናቱ ግኝት፣ እ.ኤ.አ በ2024 የባህር በር አልባነት ያስከተለው ኪሳራ ከኢትዮጵያ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ውስጥ ከ13 እስከ 23 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ይይዛል።
ይህ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና የመጣው የወደብ ኪራይ ወጪን ጨምሮ፣ በሎጂስቲክስ መጓተት ምክንያት የሚባክኑ የንግድ ዕድሎችና የትራንስፖርት ወጪዎች ተደምረው መሆኑን ተመራማሪዎቹ ገልጸዋል።
የጥናቱ ውጤት በኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ አመራሮች በተገመገመበት ወቅት፣ ኢትዮጵያ የራሷ የባህር በር እንዲኖራት የምታቀርበው ጥያቄ ከሉዓላዊነት ባለፈ ለኢኮኖሚ ዕድገቷ እጅግ አስፈላጊ መሆኑ አፅንዖት ተሰጥቶበታል።
ይህ ጥናት ኢትዮጵያ በቀጠናው ያላትን የንግድ ተወዳዳሪነት ለማሳደግና የኢኮኖሚ ጫናዋን ለመቀነስ፣ አስተማማኝና ሉዓላዊ የወደብ አማራጭ ማግኘት አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን የሚያመላክት እንደሆነም ተጠቁሟል።@SECO


