የጣሊያኑ የኢነርጂ ግዙፍ ኩባንያ ኢኒ በኮትዲቩዋር የባህር ዳርቻ እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው የተፈጥሮ ጋዝ እና ኮንደንሴት ማግኘቱን ይፋ አደረገ።
“ካላኦ ሳውዝ” የተሰኘውና በብሎክ CI-501 ውስጥ የተገኘው ይህ ክምችት፣ በሀገሪቱ ታሪክ በስፋቱ ሁለተኛው ግዙፍ የሃይድሮካርቦን ግኝት ሆኖ ተመዝግቧል።
እንደ ኩባንያው ግምት ከሆነ፣ ክምችቱ እስከ ሦስት ትሪሊዮን ኩቢክ ጫማ የሚደርስ ጋዝ እና 100 ሚሊዮን በርሜል ኮንደንሴት ይዟል ተብሎ ይታመናል።
ይህ አዲስ ግኝት ኮትዲቩዋር ያላትን የኢነርጂ አቅም በእጅጉ የሚያጠናክር ሲሆን፣ ለሀገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች፣ ለኢንዱስትሪ ዕድገት እና ለጎረቤት ሀገራት የሚላኩ ምርቶችን ለማሳደግ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ተጠቁሟል።
ኢኒ በዘርፉ 90 በመቶ ድርሻ ያለው ሲሆን፣ ቀሪውን 10 በመቶ የኮትዲቩዋር የመንግስት የነዳጅ ኩባንያ ይዟል።
ፍለጋው የተካሄደው በዘመናዊው “ሳይፔም ሳንቶሪኒ” ቁፋሮ መርከብ አማካኝነት ከ5,000 ሜትር በላይ ጥልቀት ውስጥ መሆኑ ታውቋል።
ኢኒ ከዚህ ቀደም “ባሌይን” በተሰኘው ግዙፍ የነዳጅ ክምችት ላይ በጀመረው ልማት ላይ አሁን የተገኘው “ካላኦ ሳውዝ” ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ተገልጿል።
ይህ ስኬት ኩባንያው በምዕራብ አፍሪካ እንደ አንጎላ፣ ጋና እና ናይጄሪያ ባሉ ሀገራት ያለውን ስትራቴጂካዊ ተፅዕኖ የሚያጠናክር ሲሆን፣ ቀጠናው ለዓለም አቀፍ የኢነርጂ ባለሀብቶች ያለውን ሳቢነት ይበልጥ እንደሚያጎላው የኩባንያው ቃል አቀባይ ገልጸዋል።@SECO


