እ.ኤ.አ በ2030 ድህነትን ለማጥፋት የተቀመጠው ግብ ተግዳሮት እንደገጠመው ተገለጸ

ዓለም አቀፍ የድህነት መለኪያ መስፈርት መሻሻሉን ተከትሎ በከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኘው የሰው ልጅ ቁጥር መጨመሩንና እ.ኤ.አ በ2030 ድህነትን ለማጥፋት የተቀመጠው ግብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየራቀ መምጣቱን የዓለም ባንክ እና የተመድ ሪፖርቶች አመለከቱ።

እ.ኤ.አ በሰኔ 2025 በወጣው አዲስ መረጃ መሠረት፣ ዓለም አቀፍ የድህነት ወለል በቀን ከ2.15 ዶላር ወደ 3 ዶላር ከፍ እንዲል ተደርጓል። በዚህም ምክንያት በከፋ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር ቀደም ሲል ይገመት ከነበረበት 677 ሚሊዮን ወደ 808 ሚሊዮን ከፍ ብሏል፤ ይህም ከዓለም ህዝብ 10 በመቶው ወይም ከአሥር ሰው አንዱ አሁንም በከፋ ድህነት ውስጥ እንደሚገኝ ያሳያል።

ለዚህ የድህነት መጠን መጨመርና ለድህነት ቅነሳ ጥረቶች መዝገም በምክንያትነት የተጠቀሱት የኮቪድ-19 ተፅዕኖ፣ የኢኮኖሚ አለመረጋጋት፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና በተለይም ከሰሃራ በታች ባለው አፍሪካ የሚታየው ደካማ የኢኮኖሚ እድገት ናቸው።

ሪፖርቱ እንደሚያመለክተው እስከ 2025 ድረስ ከዓለም የከፋ ድሆች መካከል ከሶስት አራተኛ በላይ የሚሆኑት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ወይም በግጭት በሚታወኩ ቀጠናዎች ውስጥ ይኖራሉ። ምንም እንኳን በዓለም አቀፍ ደረጃ የማህበራዊ ጥበቃ ተጠቃሚዎች ቁጥር ለመጀመሪያ ጊዜ ከግማሽ በላይ (52.4 በመቶ) ቢደርስም፣ አሁንም 3.8 ቢሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ምንም ዓይነት የማህበራዊ ዋስትና ድጋፍ እንደማያገኝ ተጠቁሟል።

ከመሬት ባለቤትነት መብት ጋር በተያያዘም ከፍተኛ ልዩነት መኖሩን ሪፖርቱ አጋልጧል። 66 በመቶ የሚሆነው ህዝብ የመሬት ይዞታዬ ዋስትና አለው ብሎ ቢያምንም፣ ህጋዊ የባለቤትነት ሰነድ ያላቸው ግን 43 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው።

ይህ ችግር በተለይ ከሰሃራ በታች ባለው አፍሪካ የከፋ ሲሆን፣ ሰነድ ያላቸው ሰዎች 15 በመቶ ብቻ መሆናቸው ተገልጿል።

ይህም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መደበኛ የፋይናንስ ብድር እንዳያገኙና መብታቸውን በህግ ለማስከበር እንዳይችሉ እንቅፋት ሆኖባቸዋል። ሪፖርቱ በማጠቃለያው፣ ድህነትን ለማጥፋት በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት የማህበራዊ ጥበቃ ሽፋንን ማሳደግ እና ለወሳኝ አገልግሎቶች የሚውል የሀብት ክፍተትን መሙላት አስቸኳይ እርምጃ እንደሚፈልግ አሳስቧል።@SECO

Related

በኤሌክትሪክ የምትንቀሳቀስ የዓለማችን ግዙፏ የዕቃ ጫኝ መርከብ

ንብረትነቷ የቻይና የሆነችውና 10 ሺህ ቶን ጭነት የመሸከም አቅም...

ሰሊጥ 21 ሺህ ብር በመሸጥ ከፍተኛ ዋጋ አስመዘገበ

ዋጋው ከቀደመው አመት 20 በመቶ ጭማሪ ሊያሳይ ችሏል ባለፉት ጥቂት...

የዓለም እድገት ወደ 2.6 በመቶ ዝቅ እንደሚል ተተነበየ

በጄኔቫ ይፋ የሆነው የተባበሩት መንግሥታት የንግድና ልማት ድርጅት (አንክታድ)...

በኒውዚላንድ በታክስ ማጭበርበር የተከሰሰችው አዛውንት በኢትዮጵያ ደካማ ኢንተርኔት ማሳበቧ ተገለፀ

ከኒውዚላንድ እየመጡ የሚገኙ ዘገባዎች እንዳመላከቱት  ከሆነ ሄለን ፉአታሃ የተባለች...

የኢራን ጦርነት የኢኮኖሚ ውድቀትን እያባባሰ ነው

ነዳጅ እና ውሀ ማጣሪያዎች እየተደበደቡ ነው። የኢራን እና እስራኤል፣ አሜሪካ...

Popular Categories