ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመቃወም፣ በዓለም አቀፍ የገቢ ዕቃዎች ላይ የጣሉትን የታሪፍ (ቀረጥ) መጠን ከነበረበት 10% ወደ 15% ከፍ ማድረጋቸውን ቅዳሜ ዕለት የካቲት 14 ቀን 2018 ዓ.ም. አስታውቀዋል።
ይህ ውሳኔ የተላለፈው የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቱ ከዚህ ቀደም ጥለውት የነበረውን ሰፊ የታሪፍ ዕቅድ ውድቅ ካደረገ ከአንድ ቀን በኋላ ነው። ፕሬዝዳንቱ በ “Truth Social” ማህበራዊ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት፣ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ “የማይረባ፣ በደንብ ያልተጻፈ እና እጅግ ጸረ-አሜሪካዊ” ሲሉ የነቀፉ ሲሆን፣ አዲሱ የ15 በመቶ ጭማሪም ወዲያውኑ ተግባራዊ እንደሚሆን ገልጸዋል።
ይህ የፕሬዝዳንቱ እርምጃ የተወሰደው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ “ዓለም አቀፍ የአደጋ ጊዜ የኢኮኖሚ ስልጣን ህግ” ታሪፍ ለመጣል ጥቅም ላይ ሊውል አይችልም በማለት ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ ነው።
ትራምፕ በውሳኔው በመቆጣት አርብ ዕለት ኮንግረስን በማለፍ የ10 በመቶ ታሪፍ የጣሉ ሲሆን፣ አሁን ግን መጠኑን ወደ ከፍተኛው የሕግ ገደብ ማለትም ወደ 15 በመቶ አድርሰውታል።
ፕሬዝዳንቱ በጽሁፋቸው “ለብዙ አስርት ዓመታት አሜሪካን ሲበዘብዙ በቆዩ አገራት ላይ ይህንን እርምጃ መውሰድ ተገቢ ነው” በማለት ውሳኔያቸውን ተከላክለዋል።
ከህግ አንጻር ሲታይ፣ አዲሱ ታሪፍ የተጣለው በ1974 የንግድ ህግ አንቀጽ 122 መሠረት ነው። ይህ የህግ ድንጋጌ ፕሬዝዳንቱ በሀገሪቱ የክፍያ ሚዛን ላይ “ከፍተኛ እና ከባድ” ችግሮች ሲያጋጥሙ እስከ 15 በመቶ የሚደርስ ቀረጥ ለ150 ቀናት እንዲጥሉ ስልጣን ይሰጣል።
ይሁን እንጂ ይህ አዲስ ታሪፍም ቢሆን በድጋሚ የህግ ተግዳሮቶች ሊገጥሙት እንደሚችሉ የህግ ባለሙያዎች እየገለጹ ይገኛሉ። የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ፕሬዝዳንቱ ቀደም ብለው በአረብ ብረት፣ በአሉሚኒየም እና በመኪና ምርቶች ላይ የጣሏቸውን ሌሎች ታሪፎች እንደማይመለከት ተመልክቷል።
የትራምፕ አስተዳደር አሜሪካን ዳግም ታላቅ የማድረግ ሂደትን ለማስቀጠል አስፈላጊ የሆኑ ህጋዊ የታሪፍ እርምጃዎችን መውሰዱን እንደሚቀጥል ፕሬዝዳንቱ በድጋሚ አረጋግጠዋል።
ይህ እርምጃ በዓለም አቀፍ የንግድ ግንኙነት ላይ ከፍተኛ መነቃቃትን የፈጠረ ሲሆን፣ በተለይም የታሪፍ ተመላሽ እንዲደረግላቸው የሚጠይቁ ግዛቶች እና የንግድ ድርጅቶች ከወዲሁ ድምጻቸውን ማሰማት ጀምረዋል።@SECO


