የኢትዮጵያ የመንግሥት ግዥ አገልግሎት ወደ ኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት እያደረገ ያለው ሽግግር በዋጋ ማረጋገጫ መረጃዎች መዘግየትና በገበያ ዋጋ መዋዠቅ ምክንያት ፈተና እየገጠመው መሆኑን አስታወቀ።
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አስማረ ይገዙ በቅርቡ በተካሄደ የምክክር መድረክ ላይ እንደገለጹት፣ በአዲሱ መመሪያ መሠረት የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የገበያ ዋጋ ትንተና መረጃን የማቅረብ ኃላፊነት ቢሰጠውም፣ ካለው ከፍተኛ የሥራ ጫና የተነሳ መረጃዎችን በፍጥነት ለማቅረብ መቸገሩ በግዥ ሂደቶች ላይ መጓተትን እየፈጠረ ይገኛል።
ይህ የመረጃ መዘግየት በሀገሪቱ ካለው የዋጋ ግሽበትና የገበያ አለመረጋጋት ጋር ተዳምሮ፣ አቅራቢዎች በጨረታ ወቅት ባቀረቡት ዋጋ ለመቀጠል እንዳይችሉና ተደጋጋሚ የዋጋ ክለሳዎች እንዲጠየቁ ምክንያት መሆኑ ተጠቅሷል።
ይህም በመንግሥት የግዥ ሰንሰለትና በበጀት አጠቃቀም ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ ችግሩን ለመፍታት ከስታቲስቲክስ አገልግሎት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ካፒታል ጋዜጣ እንደዘገበው ፣ አገልግሎቱ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ከአሮጌ ንብረቶችና ተሽከርካሪዎች ሽያጭ 208 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ያስታወቀ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ153 በመቶ ዕድገት ያሳየ መሆኑን ገልጿል።@SECO


