በኢቢቪ ዘጋቢ
በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ውስጥ እየታየ ያለው ከፍተኛ የገበያ መዋጥ፣ አነስተኛ ባንኮች በገበያው ውስጥ ለመቆየት ብርቱ ትግል እንዲያደርጉ እያስገደዳቸው መሆኑ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው የ2017 ዓ.ም. የፋይናንስ መረጋጋት ሪፖርት መሠረት፣ በግዙፍ እና በአነስተኛ ባንኮች መካከል ያለው የተቀማጭ ገንዘብ እና የሀብት ቁጥጥር ልዩነት እየሰፋ መምጣቱ የባንኮችን ውህደት አስፈላጊነት አጉልቶታል።
ሪፖርቱ እንደሚያሳየው፣ ምንም እንኳን አጠቃላይ የባንክ ዘርፉ እያደገ ቢሆንም፣ ጥቅሙ ግን በጥቂት ግዙፍ ባንኮች እጅ ላይ እየተከማቸ ነው። በሀገሪቱ ብቸኛው “ግዙፍ ባንክ” ተብሎ የተፈረጀው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በከፍተኛ ፍጥነት የገበያ ድርሻውን በማስፋት በአሁኑ ወቅት የጠቅላላ የባንክ ሀብቱን 49.1 በመቶ እና የጠቅላላ የተቀማጭ ገንዘቡን 48.1 በመቶ ተቆጣጥሯል።
በ”አነስተኛ ባንክ” ዘርፍ ውስጥ ለሚገኙ 25 ባንኮች፣ አስተማማኝ የገንዘብ ምንጭ ማግኘት እጅግ ፈታኝ እየሆነባቸው መጥቷል።
ደንበኞች ይበልጥ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ሰፊ የዲጂታል አገልግሎት ወዳለው ግዙፍ ባንክ በማዘንበላቸው፣ አነስተኛ ባንኮች የነበራቸው የተቀማጭ ገንዘብ ድርሻ እንዲቀንስ አድርጎታል።
ብሔራዊ ባንክ እንደገለጸው፣ የንግድ ባንክ የካፒታል ድርሻ ካለፈው ዓመት ከነበረበት 24.2 በመቶ ወደ 43.1 በመቶ በማደጉ፣ ባንኩ የተሻሉ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን ለማቅረብና የሥራ ማስኬጃ ወጪዎችን ለመቋቋም አስችሎታል። ይህ ደግሞ አነስተኛ ባንኮች በገበያው ውስጥ የሚኖራቸውን የመወዳደር አቅም አጥብቦባቸዋል።
ይህ ጫና በገበያ ድርሻ ላይ ብቻ ሳይሆን በባንኮቹ የመቋቋም አቅም ላይም ታይቷል።
ብሔራዊ ባንክ ባደረገው ምርመራ፣ “10 ትላልቅ ተቀማጮች ገንዘባቸውን በአንድ ጊዜ ቢያወጡ” በሚል በተደረገ ሙከራ፣ ከ31 ባንኮች ውስጥ 16ቱ ፈተናውን ማለፍ አልቻሉም። እነዚህም ባንኮች በሙሉ ማለት ይቻላል እንደ ግዙፍ ባንኮች ጠንካራ የገንዘብ ክምችት የሌላቸው የግል አነስተኛ እና መካከለኛ ባንኮች ናቸው።
በእዮብ ተካልኝ የሚመራዉ ተቆጣጣሪዉ ባንኩ የ”ብርቱው ፉክክር አነስተኛ ባንኮች በሀብት፣ በብድርና በተቀማጭ ገንዘብ ያላቸውን የገበያ ድርሻ እንዲያጡ አስገዳጅ ሆኗል ፤ ይህም ባንኮቹ የግዙፉን ባንክ የበላይነት ለመቋቋም እንዲችሉ የባንኮች ውህደትን እንዲያስቡ እያደረገ ነው” ብሏል።
ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ክፍት እያደረገችና የውጭ ባንኮች እንዲገቡ እየፈቀደች ባለችበት ወቅት፣ አነስተኛ ባንኮች ለመኖር ያላቸው አማራጭ እርስ በእርስ መዋሃድ ብቻ እንደሆነ ይጠቁማል።
በአሁኑ ወቅት ግዙፉ ባንክ የሀገሪቱን የብድርና የቦንድ ገበያ 51 በመቶ በላይ በመቆጣጠሩ፣ አነስተኛ ባንኮች ትላልቅ የኮርፖሬት ደንበኞችን ለማግኘት እየተቸገሩ ይገኛሉ።
ተንታኞች እንደሚተነብዩት በሚቀጥሉት 12 እና 24 ወራት ውስጥ በዘርፉ በርካታ “አስገዳጅ ውህደቶች” ሊታዩ ይችላሉ።
አነስተኛ ባንኮች ሀብታቸውን በማቀናጀት ለቴክኖሎጂ እና ለካፒታል የሚያስፈልጋቸውን አቅም በመገንባት አሁን ያለውን የገበያ መከማቸት መጋፈጥ ይችላሉ።@SECO


