የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፣ የኢትዮጵያ የመንግሥትና የግል ዘርፍ ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ተቋማት የያዙት የ529 ቢሊዮን ብር ሃብት በሀገሪቱ የፋይናንስ ሥርዓት ላይ “ሥር የሰደደ ስጋት” ሊፈጥር እንደሚችል አስጠነቀቀ።
ባንኩ እንዳመለከተው፣ የሁለቱ ተቋማት ጥሬ ገንዘብና ኢንቨስትመንት በአንድ ዓመት ውስጥ በ26 በመቶ በማደግ አጠቃላይ የፋይናንስ ሥርዓቱን 10 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ መያዝ ችሏል።
ይሁን እንጂ ከዚህ ከፍተኛ ሃብት ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው በመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድ ላይ ብቻ የዋለ መሆኑ፣ ተቋማቱ ከመንግሥት የፋይናንስ አቅም ጋር ያላቸውን ጥብቅ ቁርኝትና ተጋላጭነት የሚያሳይ መሆኑ ተገልጿል።
ይህ በመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድ ላይ የተመሠረተ የኢንቨስትመንት ክምችት፣ መንግሥት ዕዳውን የመክፈል አቅሙ ቢዳከም ወይም የዋጋ ግሽበት የገንዘቡን የመግዛት አቅም ቢሸረሽረው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የጡረታ ቁጠባ አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል ባንኩ በአጽንኦት ጠቁሟል።
መንግሥት ለሥራ ማስኬጃ የሚሆነውን ዝቅተኛ ወለድ ያለው ብድር የሚያገኘው ከእነዚህ የጡረታ ፈንዶች በመሆኑ፣ በመካከላቸው ያለው መዋቅራዊ መሳሳብ በማኅበራዊ ዋስትና ሥርዓቱ ላይ የሚፈጠር ማንኛውም መስተጓጎል በጠቅላላው የፋይናንስ ዘርፍ ላይ የሰንሰለት ተጽዕኖ ሊያሳርፍ እንደሚችል ተመላክቷል።
ብሔራዊ ባንክ ይህንን ስጋት ለመቆጣጠር በባንኮች ኢንቨስትመንት፣ በውጭ ባንኮች የፍቃድ አሰጣጥና መሰል ጉዳዮች ላይ አዳዲስ መመሪያዎችን በማውጣት የፋይናንስ ዘርፉን ቁጥጥር እያጠናከረ መሆኑን ገልጿል።@SECO


