የዓለም ባንክ ግሩፕ በምስራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር ፕሮግራም ስር በሚተገበረው የኢትዮጵያ-ኬንያ የከፍተኛ ቮልቴጅ መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክት ላይ “የተመሳጠረ እና የማጭበርበር ድርጊት” ፈጽመዋል ያላቸውን የፒ.ደብሊው.ሲ (PwC) ቅርንጫፍ ኩባንያዎች ለ21 ወራት ከማንኛውም የባንኩ ፕሮጀክቶች ማገዱን አስታውቋል።
በእገዳው የተመቱት በሞሪሸስ የሚገኘው ፒ.ደብሊው.ሲ አሶሺየትስ አፍሪካ፣ ፒ.ደብሊው.ሲ ኬንያ እና ፒ.ደብሊው.ሲ ሩዋንዳ ሲሆኑ፣ ውሳኔው የተላለፈው ኩባንያዎቹ እ.ኤ.አ. በ2019 በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል እና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የንብረት ግመታና የሂሳብ አያያዝ አማካሪነት ጨረታዎችን ለማሸነፍ በሚስጥር መያዝ ያለባቸውን የጨረታ መረጃዎች ካልተገባ መንገድ ማግኘታቸው በመረጋገጡ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ ፒ.ደብሊው.ሲ አሶሺየትስ አፍሪካ በውል አፈጻጸም ወቅት የባለሙያዎችን ብቃት፣ ዝግጁነት እና የስራ ሁኔታ አስመልክቶ የተሳሳተ መረጃ ማቅረቡና ንዑስ ተቋራጮችን ሙሉ በሙሉ አለማሳወቁ በምርመራ ተደርሶበታል።
ይህ ድርጊት በባንኩ የአማካሪዎች መመሪያ መሠረት ከፍተኛ የሥነ-ምግባር ጥሰት ሆኖ ተመዝግቧል።
ሆኖም ኩባንያዎቹ ጥፋታቸውን አምነው በመቀበላቸው፣ የውስጥ ምርመራ በማካሄዳቸው እና ከባንኩ ጋር ለመተባበር በመስማማታቸው የእገዳው ጊዜ እንዲቀነስ ተደርጓል። ይህም ሆኖ የተጣለው እገዳ በሌሎች ዓለም አቀፍ የልማት ባንኮች ዘንድም ተፈጻሚነት ሊኖረው እንደሚችል ተገልጿል።
ይህ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ ለኬንያ ኃይል በመሸጥ የውጭ ምንዛሬ ገቢ እንድታገኝ እና ኬንያም የኤሌክትሪክ አቅርቦቷን በቅናሽ ዋጋ እንድታሳድግ ታስቦ የተዘረጋ ግዙፍ ቀጠናዊ ፕሮጀክት ነው። ኩባንያዎቹ ከእገዳው ለመፈታት በባንኩ የተቀመጡ የቅንነት እና የታማኝነት መመሪያዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።@SECO


