በኢቢቪ ዘጋቢ
የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን፣ በቅርቡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በጸደቀው የፌዴራል የገቢ ግብር መመሪያ ማሻሻያ ላይ ያለውን ከፍተኛ ተቃውሞ ገለጸ።
ፌዴሬሽኑ በተለይም በባንክ ሠራተኞች የቤትና የተሽከርካሪ ብድር ወለድ ልዩነት ላይ የተጣለው የ35 በመቶ የገቢ ግብር ፍትሐዊ ስላልሆነ በአስቸኳይ እንዲሰረዝ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አቤቱታ አቅርቧል።
ውዝግቡ የተቀሰቀሰው አዲሱ መመሪያ፣ ባንኮች ለሠራተኞቻቸው የሚሰጡትን ዝቅተኛ ወለድ (7 በመቶ) እና በብሔራዊ ባንክ የተቀመጠውን መደበኛ የማበደሪያ ወለድ (15 በመቶ) መካከል ያለውን የ8 በመቶ ልዩነት እንደ “ተጨማሪ ገቢ” በመቁጠር ግብር እንዲከፈልበት በመወሰኑ ነው።
ፌዴሬሽኑ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለብሔራዊ ባንክ እና ለገንዘብ ሚኒስቴር በላከው ደብዳቤ፣ ይህ አሠራር ሠራተኛው እጁ ላይ የሚደርሰውን ገቢ እጅግ አነስተኛ እንደሚያደርገው አስረድቷል።
የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ደስታ በርሄ እንደገለጹት፣ የፋይናንስ ዘርፍ ሠራተኞች ቀድሞውኑ 35 በመቶ የገቢ ግብር፣ 7 በመቶ የጡረታ መዋጮ እና የብድር ዕዳ ክፍያ የሚፈጽሙ በመሆኑ፣ አዲሱ ታክስ ሲታከልበት አንድ ሠራተኛ ከጠቅላላ ደመወዙ የሚያገኘው 14.67 በመቶ ብቻ ነው።
ይህ ሁኔታ ሠራተኞች አሁን ያለውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም በሚያደርጉት ጥረት ላይ ትልቅ እንቅፋት መሆኑንና ምርታማነትን እንደሚቀንስ ፕሬዝዳንቱ አክለው ገልጸዋል።
በተጨማሪም ፌዴሬሽኑ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ኢትዮ ቴሌኮም ያሉ ታላላቅ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሠራተኞች ተመሳሳይ ጥቅማ ጥቅሞችን ያለ ታክስ እያገኙ መሆኑን በመጥቀስ፣ በፋይናንስ ዘርፉ ላይ ብቻ እንዲህ ዓይነት ጫና መፈጠሩ አድልዎ ያለበት አሠራር ነው ሲል ወቅሷል።
በመሆኑም መንግሥት የሠራተኛውን መሰረታዊ ፍላጎት ግምት ውስጥ በማስገባት የታክስ መመሪያውን እንዲያሻሽል ወይም ሙሉ በሙሉ እንዲሰርዝ ጥሪ አቅርቧል።@SECO


