በኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ውስጥ የሚስተዋለውን የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ለመፍታት በባንኮች፣ በአምራቾች እና በምርት ገዢዎች መካከል የተቀናጀ የሦስትዮሽ ስምምነት ሊተገበር እንደሚገባ ባለሀብቶችና የዘርፉ ባለሙያዎች ጥሪ አቀረቡ።
ይህ ጥሪ የቀረበው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በልዩ ኢኮኖሚ ዞን ዉስጥ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ከተሰማሩ ባለሀብቶች ጋር ባካሄደው የምክክር መድረክ ላይ ሲሆን፣ በተለይም በሀገር ውስጥ አምራቾች ላይ የሚታየውን የካፒታል እጥረት ለመቅረፍ እንዲህ ያለው አሰራር ወሳኝ መሆኑ ተገልጿል።
የቂሊንጦ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ዉስጥ የፋርማሲዩቲካል (የመድኃኒት) አምራች ተወካይ እንደገለጹት፣ መንግስት የሀገር ውስጥ አምራቾችን ለማበረታታት ከ5 እስከ 7 ዓመታት የሚቆይ የምርት ግዢ ዋስትና ቢሰጥም፣ ይህ ዋስትና በባንኮች ዘንድ እንደ መያዣ አለመቆጠሩ አምራቾችን ለከፍተኛ ችግር ዳርጓቸዋል።
አንድ አምራች ፋብሪካ ገንብቶ፣ ማሽነሪ አስገብቶና ሰራተኛ አሰልጥኖ ወደ ምርት ሲገባ የሚገጥመው ትልቁ ግድግዳ የሥራ ማስኬጃ ፋይናንስ (Working Capital) ማጣት መሆኑን የገለጹት ተወካዩ፣ አምራቹ የመንግስት የግዢ ዋስትና እያለውም ባንኮች ተጨማሪ የንብረት መያዣ መጠየቃቸው ምርታማነትን እየገታው መሆኑን አስረድተዋል።
ተወካዩ አምራቾችን፣ ባንኮችን እና ገዢዎችን (እንደ EPSS ወይም IPDC ያሉ) የሚያሳትፍ “የሦስትዮሽ ስምምነት” (Tri-Party Agreement) እንዲኖር ጠይቀዋል።
በዚህ አሰራር መሠረት ገዢው ተቋም ምርቱን ከአምራቹ ለመግዛት በገባው ውል መሠረት ክፍያውን በቀጥታ ለአምራቹ የብድር ባንክ ገቢ ለማድረግ ዋስትና ሲሰጥ፣ ባንኩ ደግሞ ይህንን የግዢ ውል እና የክፍያ ዋስትና እንደ ዋና መያዣ በመቁጠር ለአምራቹ አስፈላጊውን የሥራ ማስኬጃ ብድር ያቀርባል፤ አምራቹም ያለምንም የፋይናንስ ስጋት ምርቱን በጥራት እና በወቅቱ የማምረት ኃላፊነት ይወስዳል።
ይህ አሰራር ባንኮች ሊያጋጥማቸው የሚችለውን የብድር ስጋት የሚቀንስ ሲሆን፣ አምራቾችም ንብረት በመያዣነት ሳያስይዙ ብድር እንዲያገኙ መንገድ ይከፍታል።
በመድረኩ ላይ የተነሳው ሌላው ወሳኝ ጉዳይ የባንኮች የአገልግሎት አሰጣጥ ብቃት ሲሆን፣ ብዙ ጊዜ የብሔራዊ ባንክ መመሪያዎች እና ማበረታቻዎች ቢወጡም በቅርንጫፍ ደረጃ ያሉ የባንክ ሰራተኞች ስለ ስፔሻል ኢኮኖሚክ ዞኖች እና ስለ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ልዩ ባህሪ ግንዛቤ የሌላቸው መሆኑ ተጠቁሟል።
ባንኮች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሲገቡ የሚመድቧቸው ባለሙያዎች የዘርፉን ችግር የተረዱ መሆን እንዳለባቸው ያሳሰቡት ባለሀብቶቹ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱ ካልተቀላጠፈ የሀገር ውስጥ አምራቾች ከአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ውድድር ሊተርፉ እንደማይችሉ አስጠንቅቀዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በበኩሉ፣ የተነሱት የፋይናንስ እና የአሰራር ችግሮች ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት እና ለብሔራዊ ባንክ እንደሚቀርቡ ገልጿል።
እንዲህ ያሉ የሦስትዮሽ ስምምነቶች እንዲተገበሩ እና የሀገር ውስጥ አምራቾች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አስፈላጊው የፖሊሲ ድጋፍ እንዲደረግ ግፊት እንደሚደረግም ታውቋል።@SECO


