አባይ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በ30 ሚሊዮን ዶላር የአግሮ-ፕሮሰሲንግ ፋብሪካ ሊገነባ ነው

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኢንቨስትመንት ክንድ የሆነው አባይ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ (AIH)፣ በ30 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ በባሕር ዳር ከተማ ግዙፍ የአግሮ-ፕሮሰሲንግ ፋብሪካ ለመገንባት ማቀዱን አስታወቀ።

 “ባሕር ዳር አግሮ-ፕሮሰሲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር” በሚል ስያሜ የሚቋቋመው ይህ ፋብሪካ፣ በዋናነት በቆሎን በማቀነባበር ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን ለገበያ እንደሚያቀርብ ተገልጿል።

ፋብሪካው በቆሎን እሴት በመጨመር ኮርን ስታርች (Corn Starch)፣ ግሉኮስ፣ ማልቶስ፣ ሃይ-ፍሩክቶስ ኮርን ሲረፕ እና ዴክስትሪን የተባሉ ምርቶችን የሚያመርት ሲሆን፣ በአካባቢው ያለውን ሰፊ የበቆሎ ምርት በግብዓትነት ለመጠቀም አልሟል።

በዓመት 300 የሥራ ቀናትን ታሳቢ በማድረግ፣ በቀን 165 ቶን ወይም በዓመት 49,500 ቶን በቆሎ የማቀነባበር አቅም እንደሚኖረው በተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (UNIDO) መረጃዎች አመልክተዋል።

የአባይ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ገበያው ሙሉቀን ለሚዲያ እንደገለጹት፣ ይህ ፕሮጀክት በክልሉ የታቀዱ አምስት አዳዲስ የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች አካል ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ወደ ምርት ምዕራፍ ለመሸጋገር ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው።

 ፕሮጀክቱ በክልሉ የግብርና ምርቶችን ወደ ኢንዱስትሪ በማሸጋገር ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወትና የውጭ ምንዛሬን ለማዳንም እንደሚያግዝ ተስፋ ተጥሎበታል።

የአማራ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አብዱ ሁሴን በሰብሳቢነት የሚመሩት ይህ የኢንቨስትመንት ፈንድ፣ ከባሕር ዳር አግሮ-ፕሮሰሲንግ በተጨማሪ በምግብ፣ በሴራሚክስ እና በእንጨት ውጤቶች ዘርፍ ሌሎች ፋብሪካዎችን ለመክፈት እየሠራ ይገኛል።

ይህ ዓይነቱ የመንግሥት የኢንቨስትመንት ሞዴል በክልሎች ደረጃ እየተስፋፋ የመጣ ሲሆን፣ መንግሥት በስትራቴጂካዊ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ያለውን ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚያጠናክር መሆኑ ተመልክቷል።@SECO

Related

አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ እና ከፍተኛ የመንግስት የስራ  ሀላፊዎች ከኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ሀላፊነታቸው ተነሱ

ድርጅቱን በቦርድ ሊቀመንበርነት ሲመሩት የነበሩት አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ፣ምክትል  ሰብሳቢ...

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 220 ቦታዎች የሊዝ ጨረታ አወጣ

​የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ በዘጠኝ ክፍለ...

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የተሰጠው የእገዳ መመሪያ ውዝግብ አስነሳ​​

በኢትዮጵያ የሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) እና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ...

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች የሦስት እርከን የደመወዝ ጭማሪ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ጸደቀ

የሀገሪቱ ግዙፉ መንግሥታዊ የፋይናንስ ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ...

አዳማ  የፈጣን ስማርት የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ መሙያ  ተጠቃሚ  ሆነች

በአለምሰገድ እስጢፋኖስ ኢትዮ ቴሌኮም በዛሬው ዕለት ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዲስ አበባ...

Popular Categories