በአለምሰገድ እስጢፋኖስ
ሶሉሽኑ ዜጎች ካሉበት ሆነው የሰነድ ማረጋገጥ፣ የውክልና ስልጣን እና የጠበቃ ፈቃድ አገልግሎት ማግኘት እንደሚያስችል ተጠቁሟል።
ካምፖኒው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከፍትህ ሚኒስቴር እና ከፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት (DARS) ጋር በመተባበር ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ድንበር ተሻጋሪ እና ዜጋ-ተኮር አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችለውን ብሄራዊ የዲጂታል ፊርማ መድረክ ቴሌሳይን (teleSign) የተሰኘ ሶሉሽን ነው ስራ ያስጀመረወረ።
የቴሌሳይን (teleSign) መጀመር በኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ ሲሆን፤ አስተማማኝ የዲጂታል ማንነት ማረጋገጫን፣ ህጋዊ ተቀባይነት ያለውን የዲጂታል ፊርማን እና ሙሉ በሙሉ ዲጂታል የሆኑ የመንግስት አሰራሮችን የያዘ ነው።
የቴሌሳይን ቢሮክራሲን በመቀነስ፣ የአገልግሎት ተደራሽነትን በማሳደግ እና ሀገራዊ የዲጂታል ተጠቃሚነትን በማስፈን ረገድ የላቀ ፋይዳ እንዳለው ተጠቁሟል።

ቴሌሳይን (teleSign) ሶሉሽን የመንግስት ተቋማትን የሚያስተሳስር እና ባህላዊ የአገልግሎት አሰጣጥን ወደ ሙሉ ዲጂታል ተሞክሮ የሚቀይር ሲሆን፤ ለሀገራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን መፋጠን የላቀ ሚና የሚጫወት ቴክኖሎጂ እንደሆነ ተነግሯል።
እንዲሁም ዜጎች ካሉበት ሆነው የሰነድ ማረጋገጥ፣ የውክልና ስልጣን እና የጠበቃ ፈቃድ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል ተብሏል።
ቴሌሳይን በዲጂታል መንገድ ከሚያከናውናቸው ዋና ዋና አገልግሎቶች መካከል የውክልና ስልጣን (Power of Attorney) ሲሆን፤ ይህም የዲያስፖራው ማህበረሰብም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚገኙ ዜጎች በአካል ኤምባሲ ወይም ቢሮ ሳይገኙ የውክልና ስልጣን ለመስጠትም ሆነ ለማንሳት ያስችላል።
በተጨማሪም ድርጅቶችና ዜጎች ማንኛውንም ህጋዊ ሰነድ ካሉበት ቦታ ሆነው በዲጂታል መንገድ እንዲያረጋግጡ የሚያስችል የሰነድ ማረጋገጥ አገልግሎትን ያካተተ ሲሆን፤ የህግ ባለሙያዎችም የጠበቃ ፈቃድ ለማውጣትና ለማደስ የሚጠቀሙበት የተቀናጀና ወረቀት-አልባ አሠራር በሶሉሽኑ ውስጥ መካተቱ ተነግሯል።
ይህ ሶሉሽን በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የታገዘ የቪዲዮ ማንነት ማረጋገጫን (Liveness Detection) እና ከብሄራዊ ዲጂታል መታወቂያ (ፋይዳ) ጋር የተቀናጀ የማንነት ማረጋገጫ ስርዓትን የሚጠቀም በመሆኑ አስተማማኝነቱ የተረጋገጠ ነው።
ሶሉሽኑ ቀደም ሲል ሳምንታትን ይፈጅ የነበረውን አሠራር ወደ ጥቂት ደቂቃዎች ዝቅ ያደረገ ሲሆን፤ ተገልጋዮች ክፍያን በቴሌብር በመፈጸም አገልግሎቱን ማግኘት ይቻላል።
ተገልጋዮች አገልግሎቱን በ teleSign App የሞባይል መተግበሪያ፣ በድረ-ገጽ ወይም በኪው አር ማስፈንጠሪያ በመጠቀም ካሉበት ቦታ ሆነው የመንግስት አገልግሎቶችን ማግኘት ይችላሉ ተብሏል።@SECO


