የአፍሪካ ኤክስፖርት-ኢምፖርት ባንክ (አፍሬክሲም) እኤአ ከ2015 ጀምሮ ለዳንጎቴ ግሩፕ በአጠቃላይ 15 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የፋይናንስ ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ።
ባንኩ ይህንን የገለጸው ሰሞኑን ለዳንጎቴ የነዳጅ ማጣሪያ ተቋም ለተፈቀደው 4 ቢሊዮን ዶላር ሲንዲኬት ብድር ውስጥ የ2.5 ቢሊዮን ዶላር ድርሻውን በዋስትና መያዙን ባበሰረበት ወቅት ነው።
የባንኩ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጆርጅ ኤሎምቢ እንደገለጹት፣ ይህ ግዙፍ ኢንቨስትመንት ባንኩ በአፍሪካውያን ለሚመሩ የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች ያለውን እምነት የሚያሳይ ነው።
“በራሳችን ላይ ኢንቨስት ስናደርግ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለሀብት ግንባታ ብቻ ሳይሆን ለአህጉሪቱ አስተማማኝና የማይበገር የወደፊት ዕጣ ፈንታ መሰረት እየጣልን ነው” ሲሉ የኢንቨስትመንቱን አስፈላጊነት አስረድተዋል።
ይህ የቅርብ ጊዜው የ2.5 ቢሊዮን ዶላር ብድር የዳንጎቴ ነዳጅ ማጣሪያ ያለበትን ነባር ዕዳዎች በማጠቃለል የፋይናንስ አቅሙን ለማጠናከርና ለቀጣይ ዕድገት እንዲዘጋጅ ይረዳዋል ተብሏል።
በቀን 650,000 በርሜል የማጣራት አቅም ያለው ይህ ተቋም፣ አፍሪካ በነዳጅ ምርቶች ራሷን እንድትችል በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ይጠበቃል።@SECO


