በኢትዮጵያ ግዙፉ የንግድ ተቋም ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ እና ዋና መሥሪያ ቤቱን ዱባይ ያደረገው “ዘ ፈርስት ግሩፕ ሆስፒታሊቲ” በኢትዮጵያ 10 ሆቴሎችን በጋራ ለመገንባትና ለማስተዳደር የሚያስችል ታሪካዊ ስምምነት ተፈራረሙ።
ስምምነቱ በናይሮቢ እየተካሄደ ባለው የ”ፊውቸር ሆስፒታሊቲ ሰሚት አፍሪካ” ላይ በይፋ ተፈርሟል።
ይህ ስትራቴጂያዊ አጋርነት በአዲስ አበባ፣ በሐዋሳ፣ በባሕር ዳር፣ በጂማ፣ በላንጋኖ እና በደንቢ የሚገነቡ ሆቴሎችን የሚያካትት ሲሆን፤ በአጠቃላይ 1,140 የመኝታ ክፍሎችን ለገበያ ያቀርባል።
ሆቴሎቹ በዓለም አቀፉ የ”ማርዮት” ብራንድ እና በሌሎች ገለልተኛ ስያሜዎች የሚመሩ ሲሆን፣ ግንባታቸውና አገልግሎት አጀማመራቸው ከ2026 እስከ 2031 ባሉት ዓመታት ውስጥ በምዕራፍ ተከፋፍሎ የሚከናወን ይሆናል።
የሚድሮክ ሆስፒታሊቲ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሰለሞን ዘውዱ እንደገለጹት፣ ይህ ትብብር የኢትዮጵያን የሆቴል ኢንዱስትሪ ከማዘመን ባለፈ የሀገር ውስጥ የሰው ኃይልን ለማልማትና የአገሪቱን የቱሪስት መዳረሻዎች ለዓለም ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል።
ዘ ፈርስት ግሩፕ ሆስፒታሊቲ በበኩሉ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ እያሳየች ያለውን የኢኮኖሚና የቱሪዝም እድገት ከግምት ውስጥ በማስገባት ወደ ገበያው መግባቱ ስልታዊ ጠቀሜታ እንዳለው አስታውቋል።@SECO


